bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
2 Chronicles 20
2 Chronicles 20
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ከዚህ በኋላ ሞዓባውያንና አሞናውያን ከጥቂት ምዑናውያን ጋር ሆነው ኢዮሣፍጥን ለመውጋት መጡ።
2
ሰዎችም መጥተው ኢዮሣፍጥን፣ “ግዙፍ ሰራዊት ሊወጋህ ከሙት ባሕር ወዲያ ካለው ከኤዶም መጥቶብሃል፤ እነሆም፣ ሐሴሶን ታማር በተባለው በዓይንጋዲ ናቸው” አሉት።
3
ኢዮሣፍጥም እጅግ ስለ ፈራ እግዚአብሔርን ለመፈለግ ፊቱን አቀና፤ በይሁዳም ሁሉ ጾም ዐወጀ።
4
የይሁዳ ሕዝብም የእግዚአብሔርን ርዳታ ይሻ ዘንድ በአንድነት ተሰበሰበ፤ ከይሁዳ ከተሞች ሁሉም እግዚአብሔርን ለመፈለግ መጡ።
5
ኢዮሣፍጥም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፣ ከአዲሱ አደባባይ ፊት ለፊት በይሁዳና በኢየሩሳሌም ጉባኤ መካከል ቆመ፤
6
እንዲህም አለ፤ “የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ በሰማይ የምትኖር አምላክ አይደለህምን? የምድር ሕዝቦችን መንግሥታት ሁሉ የምትገዛ አንተ ነህ፤ ኀይልና ሥልጣን በእጅህ ነው፤ ሊቋቋምህም የሚችል ማንም የለም።
7
አምላካችን ሆይ፤ የዚህችን ምድር ነዋሪዎች ከሕዝብህ ከእስራኤል ፊት አሳድደህ ያስወጣህና ለወዳጅህ ለአብርሃም ዘሮች ለዘላለም የሰጠሃቸው አንተ አይደለህምን?
8
እነርሱም ተቀመጡባት፤ ለስምህ መቅደስ ሠሩባት፤ እንዲህም አሉ፤
9
‘የፍርድ ሰይፍም ሆነ የቸነፈር ወይም የራብ መከራ ቢደርስብን፣ ስምህ በተጠራበት በዚህ ቤተ መቅደስ ፊት ለፊት፣ በፊትህ ቆመን በጭንቀታችን ወደ አንተ እንጮሃለን፤ አንተም ትሰማናለህ፤ ታድነናለህም።’
10
“እስራኤል ከግብፅ በወጡ ጊዜ፣ ግዛታቸውን እንዳይወርሩባቸው በማድረግህ ከእነርሱ ተመልሰው ሳያጠፏቸው የቀሩት የአሞን፣ የሞዓብና የሴይር ተራራ ሰዎች እነሆ እዚህ አሉ።
11
እነሆ፣ አንተ ርስት አድርገህ ከሰጠኸን ምድር እኛን በማፈናቀል ወሮታ ሊመልሱልን መጥተዋል።
12
አምላካችን ሆይ፤ አንተ አትፈርድባቸውምን? የመጣብንን ይህን ታላቅ ሰራዊት እንቋቋም ዘንድ ዐቅም የለንምና የምናደርገውን አናውቅም፤ ነገር ግን ዐይኖቻችን ወዳንተ ናቸው።”
13
የይሁዳ ሰዎች ሁሉ ከሚስቶቻቸው፣ ከልጆቻቸውና ከሕፃኖቻቸው ጋር በእግዚአብሔር ፊት ቆመው ነበር።
14
በዚህ ጊዜ የአሳፍ ዘር በሆነው በሌዋዊው በዘካርያስ ልጅ፣ በየሕዚኤል ላይ የእግዚአብሔር መንፈስ መጣ። ዘካርያስም የበናያስ ልጅ ሲሆን፣ በናያስም የማታን ልጅ የሆነው የይዒኤል ልጅ ነው።
15
እርሱም እንዲህ አለ፤ “ንጉሥ ኢዮሣፍጥ፣ እናንተም በይሁዳና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሁሉ አድምጡ! እግዚአብሔር እንዲህ ይላችኋል፤ ‘ውጊያው የእግዚአብሔር እንጂ የእናንተ አይደለምና፣ ከዚህ ታላቅ ሰራዊት የተነሣ አትፍሩ፣ አትደንግጡ፣
16
ነገ በእነርሱ ላይ ውረዱ፤ እነርሱ በጺጽ መተላለፊያ ሽቅብ ይወጣሉ፣ እናንተም በይሩኤል ምድረ በዳ ውስጥ በሸለቆው መጨረሻ ላይ ታገኟቸዋላችሁ።
17
ይህን ጦርነት የምትዋጉት እናንተ አይደላችሁም፤ ይሁዳና ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ቦታ ቦታችሁን ያዙ፤ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እግዚአብሔር የሚሰጣችሁንም ማዳን እዩ። አትፍሩ፤ አትደንግጡም፤ ነገውኑ ውጡና ግጠሟቸው፤ እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ይሆናል።’ ”
18
ኢዮሣፍጥ በግንባሩ ወደ መሬት ተደፋ፤ የይሁዳና የኢየሩሳሌምም ሕዝብ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ወደቁ፤ ሰገዱም።
19
ከቀዓትና ከቆሬ ወገኖች ጥቂት ሌዋውያንም ቆመው፣ እጅግ ከፍ ባለ ድምፅ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገኑ።
20
በማግስቱም ጧት በማለዳ ተነሥተው ወደ ቴቁሔ ምድረ በዳ ሄዱ። መንገድ እንደ ጀመሩም ኢዮሣፍጥ ቆሞ፣ “ይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ፣ አድምጡኝ! በአምላካችሁ በእግዚአብሔር እመኑ፤ ትጸኑማላችሁ። በነቢያቱም እመኑ፤ ይሳካላችሁማል” አላቸው።
21
ከሕዝቡም ጋር ከተመካከረ በኋላ ከሰራዊቱ ፊት ቀድመው በመሄድ፣ “ እግዚአብሔርን አመስግኑ፣ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራልና” እያሉ ለእግዚአብሔር የሚዘምሩና ስለ ቅድስናውም ክብር የሚያወድሱ ሰዎችን መደበ።
22
መዘመርና ማወደስ እንደ ጀመሩም፣ እግዚአብሔር ይሁዳን በወረሩት በአሞን፣ በሞዓብና በሴይር ተራራ ሰዎች ላይ ድብቅ ጦር አመጣባቸው፤ ተሸነፉም።
23
የአሞንና የሞዓብ ሰዎችም የሴይርን ተራራ ሰዎች ለማጥፋትና ለመደምሰስ ተነሡባቸው። ከሴይር የመጡትን ሰዎች ካጠፉ በኋላም፣ እርስ በርስ ተጠፋፉ።
24
የይሁዳ ሰዎች ምድረ በዳውን ቍልቍል ወደሚያሳየው ቦታ መጥተው ግዙፉን ሰራዊት ሲመለከቱ፣ መሬቱ ሬሳ በሬሳ ሆኖ አዩ፤ አንድም ሰው አላመለጠም።
25
ኢዮሣፍጥና ሰዎቹም ምርኳቸውን ለማጋዝ ሄዱ፤ በዚያም መካከል እጅግ ብዙ መሣሪያና ልብስ፣ ሊሸከሙ ከሚችሉትም በላይ ውድ ዕቃዎችን አገኙ። ምርኮውም ከመብዛቱ የተነሣ ለመሰብሰብ ሦስት ቀን ፈጀ።
26
በአራተኛውም ቀን እግዚአብሔርን ባመሰገኑበት በበረከት ሸለቆ ተሰበሰቡ፤ ያም ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ የበረከት ሸለቆ ተብሎ የተጠራው ከዚህ የተነሣ ነው።
27
እግዚአብሔር በጠላቶቻቸው ላይ እንዲደሰቱ ስላደረጋቸው፣ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች ሁሉ በኢዮሣፍጥ እየተመሩ፣ በታላቅ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።
28
ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ እንደ ገቡም በበገና፣ በመሰንቆና በመለከት ድምፅ ታጅበው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አመሩ።
29
እግዚአብሔር የእስራኤልን ጠላቶች እንዴት እንደ ተዋጋቸው በሰሙ መንግሥታት ሁሉ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ፍርሀት ወደቀባቸው።
30
አምላኩ በየአቅጣጫው ዕረፍት ስለ ሰጠው፣ የኢዮሣፍጥ መንግሥት ሰላም አግኝቶ ነበር።
31
ኢዮሣፍጥ በይሁዳ ላይ ነገሠ። መንገሥ በጀመረ ጊዜም ዕድሜው ሠላሳ አምስት ዓመት ሲሆን፣ በኢየሩሳሌም ተቀሞጦ ሃያ አምስት ዓመት ገዛ። እናቱም የሺልሒ ልጅ ዓዙባ ነበረች።
32
እርሱም በአባቱ በአሳ መንገድ ሄደ፤ ከዚያም ፈቀቅ አላለም፤ በእግዚአብሔርም ፊት መልካም የሆነውን ነገር አደረገ።
33
ያም ሆኖ ግን ማምለኪያ ኰረብታዎች ሙሉ በሙሉ አልተወገዱም፤ ሕዝቡም ገና ልቡን በአባቶቹ አምላክ ላይ አልጣለም ነበር።
34
በኢዮሣፍጥ ዘመነ መንግሥት ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የተከናወኑት ሌሎች ተግባራት የአናኒ ልጅ ኢዩ በዘገበው የእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቧል።
35
ከዚህ በኋላ የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ሥራው እጅግ ክፉ ከሆነው ከእስራኤል ንጉሥ ከአካዝያስ ጋር የስምምነት ውል አደረገ፤
36
የንግድ መርከብ ለመሥራትም ተስማሙ፤ መርከቦቹንም በዔጽዮንጋብር አሠሩ።
37
የመሪሳ ሰው የሆነው የዶዳያ ልጅ አልዓዛር በኢዮሣፍጥ ላይ፣ “ከአካዝያስ ጋር የስምምነት ውል ስለ አደረግህ፣ እግዚአብሔር ሥራህን ያፈርሰዋል” ሲል ትንቢት ተናገረበት፤ መርከቦቹም ተሰበሩ፤ ለንግዱም ሥራ መንቀሳቀስ አልቻሉም።
← Chapter 19
Chapter 21 →