bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
1 Samuel 29
1 Samuel 29
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ፍልስጥኤማውያን ሰራዊታቸውን ሁሉ በአፌቅ ሰበሰቡ፤ እስራኤላውያንም በኢይዝራኤል ሸለቆ ባለው ምንጭ አጠገብ ሰፈሩ፤
2
የፍልስጥኤማውያን ገዦች በመቶና በሺሕ ሆነው ሲዘምቱ፣ ዳዊትና ሰዎቹም ከአንኩስ ጋር ደጀን ሆነው ይከተሉ ነበር።
3
የፍልስጥኤም አዛዦችም፣ “እነዚህ ዕብራውያን እዚህ ምን እያደረጉ ነው?” ብለው ጠየቁ። አንኩስም፣ “ይህ የእስራኤል ንጉሥ የሳኦል አገልጋይ የነበረው ዳዊት አይደለምን? ከእኔ ጋር መኖር ከጀመረ እነሆ ዓመት ዐለፈው፤ እኔን ከተጠጋበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ምንም በደል አላገኘሁበትም” አላቸው።
4
የፍልስጥኤማውያን አዛዦች ግን በአንኩስ ላይ ተቈጥተው እንዲህ አሉ፤ “ይህን ሰው ወደዚያው ወደ ሰጠኸው ቦታ ይመለስ ዘንድ ስደደው፤ በውጊያው ጊዜ በእኛ ላይ ተመልሶ ጠላት እንዳይሆን፣ አብሮን ወደ ጦርነቱ መሄድ የለበትም፤ የእኛን ሰዎች ራስ ቈርጦ ካልወሰደ ከጌታው ጋር እንዴት ሊታረቅ ይችላል?
5
በዘፈን እየተቀባበሉ፣ “ ‘ሳኦል ሺሕ ገደለ፤ ዳዊት ግን ዐሥር ሺሕ’ ብለው የዘመሩለት ይኸው ዳዊት አይደለምን?”
6
ስለዚህ አንኩስ ዳዊትን ጠርቶ እንዲህ አለው፤ “ሕያው እግዚአብሔርን! አንተ ታማኝ ነህ፤ ወደ እኔ እዚህ ከመጣህበት ቀን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ምንም ጥፋት ያላገኘሁብህ ስለሆነ፣ አብረኸኝ ብትዘምት በበኩሌ ደስተኛ ነበርሁ፤ ነገር ግን ገዦቹ አልተቀበሉህም፤
7
እንግዲህ ተመልሰህ በሰላም ሂድ፤ የፍልስጥኤማውያንን ገዦች ደስ የማያሰኝ ምንም ነገር አታድርግ።”
8
ዳዊትም፣ “ለመሆኑ ምን አደረግሁ? እዚህ ከመጣሁበት ዕለት ጀምሮ እስካሁን ድረስ፣ በአገልጋይህ ላይ ምን አገኘህበት? ታዲያ፣ ከንጉሡ ከጌታዬ ጠላቶች ጋር የማልዋጋው ስለ ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀው።
9
አንኩስም እንዲህ አለው፤ “በእኔ ዘንድ እንደ እግዚአብሔር መልአክ መልካም እንደ ሆንህ ዐውቃለሁ፤ የፍልስጥኤማውያን አዛዦች ግን፣ ‘አብሮን ለጦርነት መውጣት የለበትም’ ብለዋል።
10
አሁንም አብረውህ ከመጡት ከጌታህ አገልጋዮች ጋር ማለዳ ተነሡ፤ በጧት ፀሓይ እንደ ወጣችም ሂዱ” አለው።
11
ስለዚህ ዳዊትና ሰዎቹ ወደ ፍልስጥኤማውያን ምድር ለመመለስ በማለዳ ተነሡ፤ ፍልስጥኤማውያንም ወደ ኢይዝራኤል ወጡ።
← Chapter 28
Chapter 30 →