bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
1 Samuel 27
1 Samuel 27
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ዳዊት ግን በልቡ፣ “ከእነዚህ ቀናት በአንዱ በሳኦል እጅ መገደሌ ስለማይቀር፣ የሚበጀኝ ወደ ፍልስጥኤማውያን ምድር መሸሽ ብቻ ነው፤ ከዚያ በኋላም ሳኦል በእስራኤል ሁሉ እኔን ማሳደዱን ይተዋል፤ እኔም ከእጁ አመልጣለሁ” ብሎ ዐሰበ።
2
ስለዚህ ዳዊትና አብረውት ያሉት ስድስት መቶ ሰዎች ተነሥተው የጌት ንጉሥ ወደ ሆነው ወደ አሜህ ልጅ ወደ አንኩስ ሄዱ።
3
ዳዊትና ሰዎቹ በጌት በአንኩስ ዘንድ ተቀመጡ፤ እያንዳንዱ ሰው ከቤተ ሰቡ ጋር ነበረ፤ ዳዊትም ከሁለቱ ሚስቶቹ ጋር፣ ከኢይዝራኤላዊቷ ከአኪናሆምና የናባል ሚስት ከነበረችው ከቀርሜሎሳዊቷ አቢግያ ጋር ነበር።
4
ሳኦልም፣ ዳዊት ወደ ጌት እንደ ሸሸ በሰማ ጊዜ፣ እርሱን ማሳደዱን ተወ።
5
ከዚያም ዳዊት አንኩስን፣ “በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ፣ በአገሪቱ ካሉት ከተሞች በአንዲቱ እኖር ዘንድ ስፍራ ይሰጠኝ፤ ስለ ምን አገልጋይህ ካንተ ጋር በንጉሥ ከተማ ይቀመጣል?” አለው።
6
ስለዚህ በዚያ ዕለት አንኩስ ጺቅላግን ሰጠው፤ ጺቅላግም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የይሁዳ ነገሥታት ይዞታ ሆነች።
7
ዳዊት በፍልስጥኤማውያን ምድር አንድ ዓመት ከአራት ወር ተቀመጠ።
8
በዚያ ጊዜም ዳዊትና ሰዎቹ ወጥተው ጌሹራውያንን፣ ጌርዛውያንንና አማሌቃውያንን ወረሩ። እነዚህ ሕዝቦች ከጥንት ጀምሮ፣ እስከ ሱርና እስከ ግብፅ ባለው ምድር ላይ ይኖሩ ነበር።
9
ዳዊትም ምድሪቱን በመታበት ጊዜ፣ ወንድም ሆነ ሴት በሕይወት አላስቀረም፤ ነገር ግን በጎችንና ላሞችን፣ አህዮችንና ግመሎችን እንዲሁም ልብሶችን ወሰደ፤ ወደ አንኩስም ተመለሰ።
10
አንኩስም፣ “ዛሬ በማን ላይ ዘመታችሁ?” ሲል በጠየቀው ጊዜ ዳዊት፣ “የዘመትነው በይሁዳ ደቡብ፣ ወይም በይረሕምኤላውያን ደቡብ፣ ወይም በቄናውያን ደቡብ ላይ ነው” በማለት ይመልስ ነበር።
11
ዳዊት “ ‘እርሱ እንዲህ አድርጓል’ ብለው ይነግሩብናል” ብሎ ስላሰበ፣ ወንድም ሆነ ሴት በሕይወት አስቀርቶ ወደ ጌት አላመጣም። በፍልስጥኤም ግዛት በኖረበት ዘመን ሁሉ፣ እንዲህ ማድረጉ የተለመደ ነበር።
12
አንኩስም በልቡ፣ “እርሱ ራሱ የገዛ ሕዝቡ የሆኑት እስራኤላውያን እጅግ እንዲጠሉት ስላደረገ፣ ለዘላለም አገልጋዬ ይሆናል” ብሎ ስላሰበ ዳዊትን አመነው።
← Chapter 26
Chapter 28 →