bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
1 Samuel 22
1 Samuel 22
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ዳዊት ከጌት ወደ ዓዶላም ዋሻ ሸሸ፤ ወንድሞቹና የአባቱ ቤተ ሰቦች ይህን በሰሙ ጊዜ፣ እርሱ ወዳለበት ወደዚያው ወረዱ።
2
የተጨነቁ፣ ዕዳ ያለባቸውና የተከፉ አራት መቶ ያህል ሰዎች፣ ወደ እርሱ ተሰባሰቡ፤ መሪያቸውም ሆነ።
3
ዳዊት ከዚያ ተነሥቶ፣ በሞዓብ ምድር ወዳለችው ወደ ምጽጳ ሄደ፤ ለሞዓብ ንጉሥ፣ “እግዚአብሔር የሚያደርግልኝን እስካውቅ ድረስ፣ አባቴና እናቴ መጥተው ካንተ ዘንድ እንዲቀመጡ ፈቃድህ ነውን?” አለው።
4
እርሱም በሞዓብ ንጉሥ ዘንድ አስቀመጣቸው፤ ዳዊት በዐምባ ውስጥ እስከ ቈየበትም ጊዜ ድረስ ከንጉሡ ዘንድ ተቀመጡ።
5
ይሁን እንጂ ነቢዩ ጋድ ዳዊትን፣ “በዐምባው ውስጥ አትቈይ፤ ሂድና ወደ ይሁዳ ምድር ግባ” አለው። ስለዚህ ዳዊት ተነሥቶ ወደ ሔሬት ጫካ ገባ።
6
ሳኦልም፣ ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩ ሰዎች መገኘታቸውን በሰማ ጊዜ፣ በጊብዓ ኰረብታ ላይ በአጣጥ ዛፍ ሥር፣ ጦሩን በእጁ ይዞ ተቀምጦ ነበር፤ ሹማምቱም ሁሉ በዙሪያው ቆመው ነበር።
7
ሳኦልም እንዲህ አላቸው፤ “እናንት የብንያም ሰዎች ስሙ! በውኑ የእሴይ ልጅ ዕርሻና የወይን ቦታ ለሁላችሁ ይሰጣችኋልን? ሁላችሁንስ ሻለቆችና የመቶ አለቆች ያደርጋችኋልን?
8
በእኔ ላይ የዶለታችሁት ለዚህ ነውን? ልጄ ከእሴይ ልጅ ጋር ቃል ኪዳን ሲያደርግ ማንም አልነገረኝም፤ ዛሬ እንደሚያደርገው ሁሉ፣ ልጄ አገልጋዬን በእኔ ላይ እንዲያደባብኝ ማነሣሣቱን ከእናንተ ስለ እኔ ተቈርቍሮ የነገረኝ ማንም የለም።”
9
ነገር ግን እዚያ ከነበሩት የሳኦል ሹማምት ጋር ቆሞ የነበረው ኤዶማዊው ዶይቅ እንዲህ አለ፣ “የእሴይ ልጅ በኖብ ወዳለው ወደ አኬጦብ ልጅ ወደ አቢሜሌክ ሲመጣ አይቻለሁ።
10
አቢሜሌክም እግዚአብሔርን ጠየቀለት፤ እንዲሁም ስንቅና የፍልስጥኤማዊውን የጎልያድን ሰይፍ ሰጠው።”
11
ከዚያም ንጉሡ፣ የአኪጦብን ልጅ ካህኑን አቢሜሌክን፣ በኖብ ካህናት የነበሩትን የአባቱን ቤተ ሰብ በሙሉ ልኮ አስጠራቸው፤ ሁሉም ወደ ንጉሡ መጡ።
12
ሳኦልም፤ “የአኪጦብ ልጅ ሆይ፤ እንግዲህ ስማ” አለው። አቢሜሌክም፣ “እሺ ጌታዬ” ብሎ መለሰ።
13
ሳኦልም፤ “ዛሬ እንደሚያደርገው ሁሉ፣ በእኔ ላይ እንዲያምፅብኝና እንዲያደባብኝ፣ እንጀራና ሰይፍ በመስጠት፣ እግዚአብሔርን ስለ እርሱ በመጠየቅ ከእሴይ ልጅ ጋር ለምን ዶለታችሁብኝ?” አለው።
14
አቢሜሌክም ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “የንጉሥ ዐማች፣ የክብር ዘቦችህ አዛዥና በቤተ ሰብህ ዘንድ እጅግ የተከበረው ዳዊትን የመሰለ ታማኝ ከአገልጋዮችህ ሁሉ ማን አለ?
15
ስለ እርሱ እግዚአብሔርን ስጠይቅስ ያ ቀን የመጀመሪያ ጊዜዬ ነበርን? ፈጽሞ አልነበረም፤ ይህን ጕዳይ በተመለከተ አገልጋይህ የሚያውቀው ምንም ነገር ስለሌለ ንጉሥ እኔን አገልጋዩን ወይም ከአባቴ ቤተ ሰብ ማንንም ጥፋተኛ አያድርግ።”
16
ንጉሡ ግን፣ “አቢሜሌክ ሆይ፤ አንተም የአባትህም ቤተ ሰብ በሙሉ በርግጥ ትሞታላችሁ” አለው።
17
ከዚያም ንጉሡ በአጠገቡ የቆሙትን ዘቦች፣ “እነዚህም የእግዚአብሔር ካህናት ከዳዊት ጋር ስላበሩ፣ ዳዊት መኰብለሉንም እያወቁ ስላልነገሩኝ ዙሩና ግደሏቸው” ሲል አዘዛቸው። የንጉሡ ሹማምት ግን እጃቸውን አንሥተው የእግዚአብሔርን ካህናት ለመምታት ፈቃደኞች አልሆኑም።
18
ንጉሡም ዶይቅን፣ “እንግዲያውስ አንተው ዙርና ካህናቱን ግደላቸው” ብሎ አዘዘው። ኤዶማዊው ዶይቅም ዞረና ገደላቸው። በዚያች ዕለት ሰማንያ አምስት የበፍታ ኤፉድ የለበሱ ካህናትን ገደለ።
19
የካህናቱንም ከተማ ኖብን በሰይፍ መታት፣ በዚያ የሚኖሩትንም ወንዶችንና ሴቶችን፣ ልጆችንና ጡት የሚጠቡ ሕፃናትን፣ እንዲሁም በሬዎችንና አህያዎችን፣ በጎችንም ሁሉ በሰይፍ ስለት ፈጃቸው።
20
የአኪጦብ ልጅ፣ የአቢሜሌክ ልጅ አብያታር ግን አምልጦ ዳዊት ወዳለበት ሸሸ።
21
እርሱም ሳኦል የእግዚአብሔርን ካህናት እንደ ገደላቸው ለዳዊት ነገረው።
22
ዳዊትም አብያታርን እንዲህ አለው፤ “ያን ዕለት ኤዶማዊው ዶይቅ እዚያ ስለ ነበር፣ ነገሩን በትክክል ለሳኦል እንደሚናገር ዐውቄአለሁ፤ ለመላው የአባትህ ቤተ ሰብ ዕልቂት ተጠያቂው እኔ ነኝ።
23
አሁንም ከእኔ ጋር ቈይ፤ አትፍራ፤ የአንተን ሕይወት የሚፈልግ የእኔን ሕይወት የሚፈልግ ነውና። አብረኸኝ በሰላም ትኖራለህ።”
← Chapter 21
Chapter 23 →