bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
1 Samuel 20
1 Samuel 20
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ከዚህ በኋላ ዳዊት በአርማቴም ካለችው ከነዋት ዘራማ ሸሽቶ ወደ ዮናታን በመሄድ፣ “ምን አድርጌአለሁ? ምን በደልስ ፈጸምሁ? አባትህ ሕይወቴን ለማጥፋት የሚፈልገውስ በፊቱ ምን ተገኝቶብኝ ነው?” ሲል ጠየቀው።
2
ዮናታንም፣ “ይህስ ከቶ አይሁንብህ፤ አትሞትም! እነሆ፤ አባቴ ትልቅም ይሁን ትንሽ ማናቸውንም ነገር አስቀድሞ ሳይነግረኝ አያደርገውም። ታዲያ አባቴ ይህን ለምን ይደብቀኛል? ነገሩ እንዲህ አይደለም” ብሎ መለሰለት።
3
ዳዊት ግን፣ “በፊትህ ሞገስ ማግኘቴን አባትህ በሚገባ ያውቃል፤ እርሱም በልቡ፤ ‘ዮናታን እንዳያዝን ይህን ማወቅ የለበትም’ ብሏል፤ ነገር ግን ሕያው እግዚአብሔርን! በነፍስህ እምላለሁ በእኔና በሞት መካከል አንድ ርምጃ ብቻ ቀርቷል” ብሎ ማለ።
4
ዮናታንም ዳዊትን፣ “እንዳደርግልህ የምትፈልገውን ማናቸውንም ነገር አደርግልሃለሁ” አለው።
5
ስለዚህ ዳዊት እንዲህ አለ፤ “እነሆ፤ ነገ የወር መባቻ በዓል ስለሆነ፣ ከንጉሡ ጋር ምሳ መብላት ይጠበቅብኛል፤ ነገር ግን እስከ ከነገ ወዲያ ማታ ድረስ ከዱር ልደበቅ፤
6
አባትህ ከፈለገኝ፣ ‘ለቤተ ዘመዶቹ ሁሉ ዓመታዊ መሥዋዕት የሚቀርብ ስለሆነ፣ ዳዊት ወደ መኖሪያ ከተማው ወደ ቤተ ከቤተ ልሔም ቶሎ ለመሄድ አጥብቆ ፈቃድ ጠየቀኝ’ ብለህ ንገረው።
7
እርሱም ‘መልካም ነው’ ካለ፣ አገልጋይህን የሚያሠጋው የለም፤ ከተቈጣ ግን፣ ክፉ ነገር እንዳሰበብኝ ታረጋግጣለህ።
8
አንተ ግን፤ ለአገልጋይህ በጎነትን አሳይ፣ ከአገልጋይህ ጋር በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን ገብታችኋልና። እኔ በደለኛ ከሆንሁ፣ አንተው ራስህ ግደለኝ፤ ለምንስ ለአባትህ አሳልፈህ ትሰጠኛለህ!”
9
ዮናታንም፣ “ይህ ከአንተ ይራቅ! አባቴ ክፉ ነገር እንዳሰበብህ ባውቅ ኖሮ እንዴት ሳልነግርህ እቀራለሁ?” አለው።
10
ዳዊትም፣ “አባትህ ክፉ ቃል ቢመልስልህ ማን ይነግረኛል?” ብሎ ጠየቀው።
11
ዮናታን፣ “በል ና፤ ወደ ሜዳ እንውጣ” አለው፤ ተያይዘውም ወጡ።
12
ከዚያም ዮናታን ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ምስክር ይሁንብኝ፤ አባቴን ነገ መርምሬ ነገ ወይም ከነገ ወዲያ በዚህ ሰዓት እልክብሃለሁ፤ ስለ አንተ ያለው አመለካከት በጎ ከሆነም አሳውቅሃለሁ።
13
ነገር ግን አባቴ ክፉ አስቦብህ፣ ይህን ሳላሳውቅህ ብቀርና በሰላም እንድትሄድ ባላደርግ፣ እግዚአብሔር ክፉ ያድርግብኝ፤ ከዚያም የባሰ ያምጣብኝ። እግዚአብሔር ከአባቴ ጋር እንደ ነበር እንደዚሁ ከአንተም ጋር ይሁን።
14
አንተም እኔ በሕይወት እስካለሁ ድረስ እንዳልገደል የእግዚአብሔርን በጎነት አድርግልኝ።
15
እግዚአብሔር የዳዊትን ጠላቶች ሁሉ ከምድረ ገጽ በሚደመስስበት ጊዜ እንኳ የበጎነት ሥራህ ከቤተ ሰቤ በፍጹም አይቋረጥ።”
16
ስለዚህ ዮናታን፣ “የዳዊትን ጠላቶች እግዚአብሔር ይፋረዳቸው” በማለት ከዳዊት ቤት ጋር ቃል ኪዳን አደረገ።
17
ዮናታን ከፍቅሩ የተነሣ ዳዊት እንደ ገና እንዲምልለት አደረገ፤ ዳዊትን የሚወድደውም እንደ ራሱ አድርጎ ነበርና።
18
ከዚያም ዮናታን ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “ነገ የወር መባቻ በዓል ነው፤ መቀመጫህ ባዶ ስለሚሆን፣ አለመኖርህ ይታወቃል።
19
ከነገ ወዲያ ምሽት ላይ ይህ ችግር በተፈጠረ ዕለት ወደ ተደበቅህበት ስፍራ ሂድና ኤዜል በተባለው ድንጋይ አጠገብ ቈይ።
20
እኔም በአንድ ዒላማ ላይ እንደሚያነጣጥር ሰው ወደ ድንጋዩ አጠገብ ሦስት ፍላጻ እወረውራለሁ፤
21
ከዚያም፣ ‘ሂድና ፍላጾቹን አምጣቸው’ ብዬ አንድ ልጅ እልካለሁ፤ ልጁንም፣ ‘እነሆ፤ ፍላጾቹ ያሉት፣ ከአንተ ወደዚህ ነው፤ ሄደህ አምጣቸው’ ያልሁት እንደ ሆነ፣ ሕያው እግዚአብሔርን! ክፉ ነገር አያገኝህም፤ አደጋም የለም፤ ውጣና ና።
22
ነገር ግን ልጁን፣ ‘እነሆ፤ ፍላጾቹ ያሉት ከአንተ ወዲያ ዐልፎ ነው’ ያልሁት እንደ ሆነ እግዚአብሔር እንድትሄድ ፈቅዷልና ሂድ።
23
አንተና እኔ ስለ ተነጋገርነው ነገር እነሆ፤ እግዚአብሔር በመካከላችን ለዘላለም ምስክር ነው።”
24
ስለዚህም ዳዊት በዱር ተደበቀ፤ የወር መባቻ በዓል በተከበረበት ጊዜ፣ ንጉሡ ግብር ለመብላት ተቀመጠ፤
25
ንጉሡ እንደ ወትሮው በግድግዳው አጠገብ ተቀመጠ፤ ዮናታን ከፊት ለፊቱ፣ አበኔር ደግሞ ከአጠገቡ ተቀመጡ፤ የዳዊት መቀመጫ ግን ባዶ ነበር።
26
ሳኦልም፣ “ዳዊት በሥርዐቱ መሠረት እንዳይነጻ የሚያደርገው አንድ ነገር ገጥሞታል፤ በርግጥም አልነጻም” ብሎ ስላሰበ፣ በዚያ ቀን ምንም አልተናገረም።
27
በማግስቱም፣ ወር በገባ በሁለተኛው ቀን የዳዊት መቀመጫ ባዶ ነበር፤ ከዚያም ሳኦል ልጁን ዮናታንን፣ “የእሴይ ልጅ ትናንትናም፣ ዛሬም ግብር ላይ ያልተገኘው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው።
28
ዮናታንም እንዲህ ብሎ መለሰለት፤ “ዳዊት ወደ ቤተ ልሔም እንዲሄድ እፈቅድለት ዘንድ አጥብቆ ለመነኝ።
29
እርሱም ‘ቤተ ሰባችን በከተማዪቱ ውስጥ መሥዋዕት ስለሚያደርግ በዚያ እንድገኝ ወንድሜ አዞኛልና ልሂድ፤ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ ወንድሞቼን ለማየት እንድሄድ አሰናብተኝ’ አለኝ። በንጉሡ ግብር ላይ ሳይገኝ የቀረውም በዚህ ምክንያት ነው።”
30
ሳኦል በዮናታን ላይ እጅግ ተቈጣ፤ እንዲህም አለው፤ “አንተ የዚያች ጠማማና ዐመፀኛ ሴት ልጅ! ለአንተው ለራስህ ውርደት፣ ለወላጅ እናትህም ዕፍረት ከሚሆነው ከእሴይ ልጅ ጋር መግጠምህን የማላውቅ መሰለህ?
31
የእሴይ ልጅ በምድር ላይ በሕይወት እስካለ ድረስ አንተም ሆንህ መንግሥትህ አትጸኑም። መሞት ስለሚገባው፣ ሰው ላክና አስመጣልኝ!”
32
ዮናታንም፣ “ለምን ይገደላል? ጥፋቱስ ምንድን ነው?” ሲል አባቱን ጠየቀ።
33
ሳኦልም ዮናታንን ለመግደል ጦሩን ወረወረበት። ስለዚህ ዮናታን፣ አባቱ ዳዊትን ለመግደል ቈርጦ መነሣቱን ዐወቀ።
34
ዮናታንም በታላቅ ቍጣ ከግብሩ ላይ ተነሣ፤ አባቱም ዳዊትን ስላዋረደው ወሩ በገባ በሁለተኛው ቀን ምግብ አልበላም።
35
በማግስቱም ጧት ዮናታን አንድ ትንሽ ልጅ አስከትሎ፣ ከዳዊት ጋር ወደ ተቃጠረበት ቦታ ሄደ፤
36
ልጁንም፣ “ሩጥ! የምሰዳቸውን ፍላጻዎች ፈልጋቸው” አለው፤ ልጁም በሮጠ ጊዜ፣ ከእርሱ አሳልፎ አንድ ፍላጻ ወረወረ።
37
ልጁም የዮናታን ፍላጻ ባረፈበት ስፍራ እንደ ደረሰ፤ ዮናታን ጠራውና፣ “ፍላጻው ካንተ ወዲያ ዐልፎ የለምን?” አለው።
38
እርሱም “ቶሎ በል! ፍጠን! አትቁም!” ሲል ጮኸበት፤ ልጁም ፍላጻዎቹን ሰብስቦ ወደ ጌታው ተመለሰ።
39
ከዮናታንና ከዳዊት በስተቀር ልጁ ስለዚህ ነገር የሚያውቀው አንዳች አልነበረም።
40
ከዚያም ዮናታን የጦር መሣሪያውን ለልጁ ሰጥቶ፣ “ይዘህ ወደ ከተማ ተመለስ” አለው።
41
ልጁ ከሄደ በኋላ፣ ዳዊት ከድንጋዩ በስተ ደቡብ ከተደበቀበት ቦታ ወጥቶ በዮናታን ፊት ሦስት ጊዜ በምድር ላይ ተደፍቶ ሰገደለት፤ ከዚያም ተሳሳሙ፤ ተላቀሱም፤ በይበልጥ ያለቀሰው ግን ዳዊት ነበር።
42
ዮናታንም ዳዊትን፤ “ ‘በአንተና በእኔ፣ በዘሮችህና በዘሮቼ መካከል እግዚአብሔር ለዘላለም ምስክር ነው’ ተባብለን ወዳጅነታችን እንዲጸና በእግዚአብሔር ስም ስለ ተማማልን እንግዲህ በሰላም ሂድ” አለው። ከዚያም ዳዊት ተነሥቶ ሄደ፤ ዮናታንም ወደ ከተማ ተመለሰ።
← Chapter 19
Chapter 21 →