bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
1 Samuel 13
1 Samuel 13
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ሳኦል በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ነበረ፤ እስራኤልንም አርባ ሁለት ዓመት ገዛ።
2
ሳኦል ከእስራኤል ሦስት ሺሕ ሰዎች መረጠ። ሁለቱ ሺሕ በማክማስና በኰረብታማው አገር በቤቴል ከሳኦል ጋር፣ አንዱ ሺሕ ደግሞ በብንያም ግዛት በጊብዓ ከዮናታን ጋር ነበሩ። የቀሩትን ሰዎች ግን ወደየቤታቸው እንዲሄዱ አሰናበተ።
3
ዮናታን ጊብዓ የነበረውን የፍልስጥኤማውያን ጦር ሰፈር መታ፤ ፍልስጥኤማውያንም ይህን ሰሙ። ሳኦልም፣ “ዕብራውያን ይስሙ!” በማለት በምድሪቱ ሁሉ መለከት አስነፋ።
4
ስለዚህ እስራኤላውያን ሁሉ፣ “ሳኦል የፍልስጥኤማውያንን ጦር ሰፈር መታ፤ እስራኤልም በፍልስጥኤማውያን ዘንድ እንደ ርኩስ ተቈጥራ ተጠላች” የሚለውን ወሬ ሰሙ፤ ሕዝቡም ሳኦልን ለመከተል ወደ ጌልገላ ተሰበሰቡ።
5
ፍልስጥኤማውያን ሦስት ሺሕ ሠረገሎች፣ ስድስት ሺሕ ፈረሰኞች ቍጥሩ እንደ ባሕር አሸዋ የበዛ ሰራዊት ይዘው እስራኤልን ለመውጋት ተሰበሰቡ፤ ወጥተውም ከቤት አዌን በስተ ምሥራቅ ባለችው በማክማስ ሰፈሩ።
6
እስራኤላውያን፣ ያሉበት ሁኔታ እጅግ የሚያሠጋ መሆኑንና ሰራዊታቸውም በከባድ ጭንቀት ውስጥ መግባቱን ባዩ ጊዜ፣ በየዋሻውና በየቍጥቋጦው፣ በየዐለቱ መካከልና በየገደሉ እንዲሁም በየጕድጓዱ ሁሉ ተደበቁ።
7
ከዕብራውያንም አንዳንዶቹ ዮርዳኖስን ተሻግረው ወደ ጋድና ወደ ገለዓድ ምድር ሄዱ። ሳኦል ግን በጌልገላ ቈየ፣ አብሮት የነበረውም ሰራዊት ሁሉ በፍርሀት ይንቀጠቀጥ ነበር።
8
እርሱም ሳሙኤል በሰጠው ቀጠሮ መሠረት ሰባት ቀን ጠበቀው። ነገር ግን ሳሙኤል ወደ ጌልገላ አልመጣም፤ የሳኦልም ሰራዊት መበታተን ጀመረ።
9
በዚህ ጊዜ ሳኦል፣ “የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕቱን አምጡልኝ” አለ። ከዚያም የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀረበ።
10
ልክ መሥዋዕቱን አቅርቦ እንዳበቃ፣ ወዲያውኑ ሳሙኤል መጣ፤ ሳኦልም ሊቀበለው ወጣ።
11
ሳሙኤልም፣ “ያደረግኸው ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። ሳኦልም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ሰራዊቱ መበታተኑን፣ አንተም በቀጠርኸው ጊዜ አለመምጣትህን፣ ፍልስጥኤማውያንም በማክማስ መሰብሰባቸውን አየሁ፤
12
‘ስለዚህ ፍልስጥኤማውያን ወርደው ወደ ጌልገላ ይመጡብኛል፤ እኔም የእግዚአብሔርን ሞገስ አልለመንሁም’ ብዬ አሰብሁ። ስለዚህ የሚቃጠል መሥዋዕት ማቅረብ ግድ ሆነብኝ።”
13
ሳሙኤልም እንዲህ አለ፤ “የማይገባህን አደረግህ፤ አምላክህ እግዚአብሔር የሰጠህን ትእዛዝ አልጠበቅህም፤ ጠብቀኸው ቢሆን ኖሮ፣ መንግሥትህን በእስራኤል ላይ ለዘላለም ባጸናልህ ነበር፤
14
አሁን ግን መንግሥትህ አይጸናም፤ እነሆ፣ እግዚአብሔር እንደ ልቡ የሚሆንለትን ሰው አግኝቷል፤ አንተ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ባለመጠበቅህም፣ እርሱን የሕዝቡ መሪ አድርጎ መርጦታል።”
15
ከዚያ በኋላ ሳሙኤል ከጌልገላ ተነሥቶ በብንያም ግዛት ወዳለው ወደ ጊብዓ ወጣ። ሳኦልም አብረውት የነበሩትን ሰዎች ቈጠራቸው፤ ብዛታቸውም ስድስት መቶ ያህል ነበረ።
16
ፍልስጥኤማውያን በማክማስ ሰፍረው በነበረበት ጊዜ ሳኦል፣ ልጁ ዮናታንና አብረዋቸው የነበሩት ሰዎች በብንያም ግዛት በምትገኘው በጊብዓ ነበሩ።
17
በሦስት ምድብ የተከፈሉ ወራሪዎች ከፍልስጥኤማውያን ሰፈር ወጡ፤ አንዱ ምድብ በሦጋል ግዛት ወደሚገኘው ወደ ዖፍራ አቀና፤
18
ሌላው ወደ ቤትሖሮን፣ ሦስተኛው ደግሞ በምድረ በዳው ትይዩ ካለው ከስቦይም ሸለቆ ቍልቍል ወደሚያሳየው ድንበር ዞረ።
19
ፍልስጥኤማውያን፣ “ዕብራውያን ሰይፍ ወይም ጦር ለራሳቸው አይሥሩ” ብለው ስለ ነበር፣ በመላው የእስራኤል ምድር ብረት ቀጥቃጭ አልተገኘም።
20
ስለዚህ እስራኤላውያን ሁሉ፣ ማረሻቸውንና ዶማቸውን ለማሾል፣ ጠገራቸውንና ማጭዳቸውን ለማሳል ወደ ፍልስጥኤማውያን ይወርዱ ነበር።
21
ማረሻና ዶማ ለማሾል የሚከፈለው ዋጋ ሁለት ሦስተኛ ሰቅል ሲሆን፣ መንሽና ጠገራ እንዲሁም የበሬ መንጃ ለማሾል ደግሞ አንድ ሦስተኛ ሰቅል ነበር።
22
ስለዚህ ጦርነቱ በተደረገበት ዕለት ከሳኦልና ከልጁ ከዮናታን በስተቀር፣ አብረዋቸው ከነበሩት ወታደሮች መካከል ሰይፍ ወይም ጦር የያዘ አንድም ሰው አልነበረም።
23
በዚያ ጊዜ አንድ የፍልስጥኤማውያን ጭፍራ ወደ ማክማስ መተላለፊያ ወጥቶ ነበር።
← Chapter 12
Chapter 14 →