bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
1 Kings 19
1 Kings 19
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
አክዓብ በዚህ ጊዜ፣ ኤልያስ ያደረገውን በሙሉ፣ ነቢያቱንም ሁሉ እንዴት በሰይፍ እንዳስገደላቸው ለኤልዛቤል ነገራት።
2
ስለዚህም እርሷ፣ “ነገ በዚህ ሰዓት ያንተንም ነፍስ ከእነዚያ እንደ አንዱ ነፍስ ሳላደርጋት ብቀር አማልክት እንዲህ ያድርጉብኝ፤ ከዚህ የባሰም ያምጡብኝ” ስትል ወደ ኤልያስ መልእክተኛ ላከች።
3
ኤልያስም ፈርቶ ስለ ነበር፣ ሕይወቱን ለማትረፍ ሲል ሸሸ። በይሁዳ ምድር ወዳለችው ወደ ቤርሳቤህ እንደ መጣም አገልጋዩን በዚያ ተወው፤
4
በምድረ በዳም ውስጥ የአንድ ቀን መንገድ ተጓዘ፤ ወደ አንድ ክትክታ ዛፍ እንደ መጣም፣ ከሥሩ ተቀምጦ፣ ይሞት ዘንድ “ እግዚአብሔር ሆይ፤ በቅቶኛል፤ እኔ ከቀደሙት አባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰዳት” ብሎ ጸለየ።
5
ከዚያም ከዛፍ ሥር ተጋደመ፤ እንቅልፍም ወሰደው። በድንገትም አንድ መልአክ ነካ አደረገውና፣ “ተነሥና ብላ” አለው።
6
ዘወር ብሎ ሲመለከትም፣ እነሆ፣ በፍም የተጋገረ ዕንጐቻና አንድ ገንቦ ውሃ ከራስጌው አገኘ፤ ከበላና ከጠጣም በኋላ ተመልሶ ተኛ።
7
የእግዚአብሔርም መልአክ እንደ ገና መጥቶ ነካ አደረገውና፣ “ሩቅ መንገድ ስለምትሄድ ተነሥና ብላ” አለው።
8
ስለዚህም ተነሥቶ በላ፤ ጠጣም፤ በምግቡም ብርታት አግኝቶ ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወደ ኮሬብ እስኪደርስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ተጓዘ፤
9
በዚያም ወደ አንዲት ዋሻ ገብቶ ዐደረ። የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እርሱ መጣ፤ “ኤልያስ ሆይ፤ እዚህ ምን ታደርጋለህ?” አለው።
10
እርሱም፣ “እኔ ለሰራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ፤ እስራኤላውያን ኪዳንህን ትተዋል፤ መሠዊያዎችህን አፍርሰዋል፤ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋልና። የቀረሁት እኔ ብቻ ነኝ፤ አሁንም እኔን ለመግደል ይፈልጋሉ” አለ።
11
እግዚአብሔርም ፣ “ እግዚአብሔር በዚያ ያልፋልና ወደ ተራራው ወጥተህ በእግዚአብሔር ፊት ቁም” አለው። ከዚያም ታላቅና ኀይለኛ ነፋስ ተራሮቹን ሰነጣጠቀ፤ ዐለቶችንም በእግዚአብሔር ፊት ብትንትናቸውን አወጣ፤ እግዚአብሔር ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም፤ ከነፋሱም ቀጥሎ የምድር መነዋወጥ ሆነ፤ እግዚአብሔር ግን በምድር መነዋወጡ ውስጥ አልነበረም።
12
ከምድር መነዋወጡም ቀጥሎ እሳት መጣ፤ እግዚአብሔር ግን በእሳቱ ውስጥ አልነበረም፤ ከእሳቱም ቀጥሎ ለስ ለስ ያለ ድምፅ ተሰማ።
13
ኤልያስም ይህን ሲሰማ፣ ፊቱን በመጐናጸፊያው ሸፍኖ ወጣና በዋሻው ደጃፍ ቆመ። ከዚያም፣ “ኤልያስ ሆይ፤ እዚህ ምን ታደርጋለህ?” የሚል ድምፅ ሰማ።
14
እርሱም፣ “እኔ ሁሉን ለሚችል ጌታ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ፤ እስራኤላውያን ኪዳንህን ትተዋል፤ መሠዊያዎችህን አፍርሰዋል፤ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋልና። የቀረሁት እኔ ብቻ ነኝ፤ አሁንም እኔን ለመግደል ይፈልጋሉ” አለ።
15
እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “በመጣህበት መንገድ ተመልሰህ ወደ ደማስቆ ምድረ በዳ ሂድ፤ እዚያ ስትደርስም አዛሄልን በሶርያ ላይ እንዲነግሥ ቅባው።
16
እንዲሁም የናሜሲን ልጅ ኢዩን በእስራኤል ላይ እንዲነግሥ ቅባው፤ ደግሞም ነቢይ ሆኖ በእግርህ እንዲተካ የአቤል ምሖላን ሰው የሣፋጥን ልጅ ኤልሳዕን ቅባው።
17
ከአዛሄል ሰይፍ ያመለጠውን ኢዩ ይገድለዋል፤ ከኢዩ ሰይፍ ያመለጠውን ደግሞ ኤልሳዕ ይገድለዋል።
18
እኔም ጕልበታቸው ለበኣል ያልተንበረከከውንና አፋቸው ምስሉን ያልሳመውን ሰባት ሺሕ ሰዎች በእስራኤል አስቀራለሁ።”
19
ስለዚህ ኤልያስ ከዚያ ተነሥቶ ሲሄድ፣ የሣፋጥን ልጅ ኤልሳዕን ዐሥራ ሁለት ጥማድ በሬ አውጥቶ ራሱ በዐሥራ ሁለተኛው ጥማድ በሬ ሲያርስ አገኘው። ኤልያስም ወደ እርሱ መጥቶ መጐናጸፊያውን በላዩ ጣለበት።
20
ከዚያም ኤልሳዕ በሬዎቹን ትቶ ኤልያስን ተከትሎ እየሮጠ፣ “አባቴንና እናቴን ስሜ እንድሰናበታቸው ፍቀድልኝ፤ ከዚያም እከተልሃለሁ” አለው። ኤልያስም መልሶ፣ “እኔ ምን ያደረግሁህ ነገር አለ? ልትመለስ ትችላለህ” አለው።
21
ስለዚህም ኤልሳዕ ትቶት ተመለሰ። ሁለቱን በሬዎቹን ወስዶ ዐረደ፤ የዕርሻ ዕቃውን አንድዶ ሥጋቸውን በመቀቀል ለሕዝቡ ሰጠ፤ እነርሱም በሉ። ከዚያም ኤልያስን ለመከተል ሄደ፤ ረዳቱም ሆነ።
← Chapter 18
Chapter 20 →