bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
1 Kings 17
1 Kings 17
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
በዚህ ጊዜ ከገለዓድ ነዋሪዎች አንዱ የሆነው ቴስብያዊው ኤልያስ አክዓብን፣ “የማመልከው ሕያው እግዚአብሔርን ፣ በእኔ ቃል ካልሆነ በቀር፣ በሚቀጥሉት ዓመታት ዝናብ ወይም ጠል አይኖርም” አለው።
2
ከዚያም እንዲህ የሚል የእግዚአብሔር ቃል ለኤልያስ መጣለት፤
3
“ከዚህ ተነሥተህ ወደ ምሥራቅ ሂድ፤ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ባለው በኮራት ወንዝ ተሸሸግ።
4
ውሃ ከወንዙ ትጠጣለህ፤ ቍራዎችም እዚያው እንዲመግቡህ አዝዣለሁ።”
5
ስለዚህ እግዚአብሔር ያዘዘውን ፈጸመ፤ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ወዳለው ወደ ኮራት ወንዝ ሄዶ በዚያ ተቀመጠ።
6
ቍራዎችም ጧትና ማታ እንጀራና ሥጋ ያመጡለት ነበር፤ ውሃም ከወንዙ ይጠጣ ነበር።
7
በምድሪቱ ላይ ዝናብ ባለመጣሉ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወንዙ ደረቀ።
8
ከዚያም እንዲህ የሚል የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤልያስ መጣ፤
9
“ተነሥና ሲዶና ውስጥ ወዳለችው ወደ ሰራፕታ ሄደህ ተቀመጥ፤ በዚያም አንዲት መበለት እንድትመግብህ አዝዣለሁ።”
10
ስለዚህ ተነሥቶ ወደ ሰራፕታ ሄደ። ወደ ከተማዪቱ በር እንደ ደረሰም፣ አንዲት መበለት ጭራሮ ስትለቃቅም አገኛት፤ ጠርቶም፣ “የምጠጣው ውሃ በዕቃ ታመጪልኛለሽን?” ሲል ለመናት።
11
ልታመጣለት ስትሄድ አሁንም ጠራትና፣ “እባክሽን፣ ቍራሽ እንጀራም ይዘሽልኝ ነይ” አላት።
12
እርሷም መልሳ፣ “አምላክህን ሕያው እግዚአብሔርን! በማድጋ ካለው ዕፍኝ ዱቄትና በማሰሮ ካለው ጥቂት ዘይት በቀር ምንም የለኝም። እነሆ፤ ለራሴና ለልጄ ምግብ አዘጋጅቼ በልተን እንድንሞት ጭራሮ ለቃቅሜ ወደ ቤት ልወስድ ነው” አለችው።
13
ኤልያስም መልሶ እንዲህ አላት፤ “አይዞሽ አትፍሪ፤ ወደ ቤት ገብተሽ እንዳልሽው አድርጊ፤ በመጀመሪያ ግን ከዚያችው ካለችሽ ትንሽ ዕንጐቻ ጋግረሽ አምጪልኝ፤ ከዚያም ለራስሽና ለልጅሽ ጋግሪ፤
14
የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ እግዚአብሔር ለምድሪቱ ዝናብ እስከሚሰጥበት ዕለት ድረስ፤ ከማድጋው ዱቄት አይጠፋም፤ ከማሰሮውም ዘይት አያልቅም።’ ”
15
እርሷም ሄዳ ኤልያስ እንደ ነገራት አደረገች፤ በዚህ ሁኔታም ኤልያስ፣ መበለቲቱና ቤተ ሰቧ ብዙ ቀን ተመገቡ፤
16
በኤልያስ በተነገረው የእግዚአብሔር ቃል መሠረት ከማድጋው ዱቄት አልጠፋም፤ ከማሰሮውም ዘይት አላለቀም ነበርና።
17
ከጥቂት ጊዜ በኋላም የባለቤቲቱ ልጅ ታመመ፤ ሕመሙ እየጠናበት ሄደ፣ በመጨረሻም ትንፋሹ ቀጥ አለ።
18
እርሷም ኤልያስን፤ “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፤ እኔ ምን አደረግሁህ? እዚህ የመጣኸው ኀጢአቴን አስታውሰህ ልጄን ለመግደል ነውን?” አለችው።
19
ኤልያስም መልሶ፣ “ልጅሽን ስጪኝ” አላት፤ ልጁንም ከዕቅፏ ወስዶ እርሱ ወደሚኖርበት ሰገነት በማውጣት በዐልጋው ላይ አስተኛው።
20
ከዚያም፣ “አምላኬ እግዚአብሔር ሆይ፤ ልጇን እንዲሞት በማድረግ ተቀብላ በምታስተናግደኝ በዚህች መበለት ላይም መከራ ታመጣባታለህን?” ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ።
21
በልጁም ላይ ሦስት ጊዜ ተዘርግቶ፣ “አምላኬ እግዚአብሔር ሆይ፤ የዚህ ልጅ ነፍስ ትመለስለት” ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ።
22
እግዚአብሔርም የኤልያስን ጩኸት ሰማ፤ የልጁም ነፍስ ተመለሰችለት፤ እርሱም ዳነ።
23
ከዚያም ኤልያስ ልጁን አስነሥቶ ከሰገነቱ ወደ ምድር ቤት አወረደው፤ ለእናቱም “ልጅሽ ይኸውልሽ፤ ድኖልሻል!” ብሎ ሰጣት።
24
ከዚያም ሴቲቱ ኤልያስን፣ “አሁን የእግዚአብሔር ሰው መሆንህን፣ ከአንደበትህም የወጣው የእግዚአብሔር ቃል እውነት መሆኑን ዐወቅሁ” አለችው።
← Chapter 16
Chapter 18 →