bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
1 Corinthians 6
1 Corinthians 6
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ከመካከላችሁ አንድ ሰው ከሌላው ጋር ሙግት ቢኖረው፣ ጕዳዩን በቅዱሳን ፊት በማቅረብ ፈንታ እንዴት ደፍሮ በማያምኑ ሰዎች ፊት ለመፋረድ ያቀርባል?
2
ቅዱሳን በዓለም ላይ እንደሚፈርዱ አታውቁምን? በዓለም ላይ የምትፈርዱ ከሆነ፣ እንግዲያው፣ በትንሹ ነገር ላይ ለመፍረድ አትበቁምን?
3
በምድራዊ ሕይወት ጕዳይ ቀርቶ፣ በመላእክት ላይ እንኳ እንደምንፈርድ አታውቁምን?
4
እንግዲህ እንዲህ ያለ ጕዳይ ሲያጋጥማችሁ፣ በቤተ ክርስቲያን የተናቁትን ሰዎች ፈራጅ አድርጋችሁ ሹሟ!
5
ይህንም የምለው ላሳፍራችሁ ብዬ ነው። ለመሆኑ ከመካከላችሁ ወንድሞችን ለማስታረቅ የሚበቃ አስተዋይ ሰው የለምን?
6
ነገር ግን ወንድም ወንድሙን ለመክሰስ ፍርድ ቤት ይሄዳል፤ ያውም በማያምኑ ሰዎች ፊት!
7
እንግዲህ በመካከላችሁ መካሰስ መኖሩ ራሱ ውድቀታችሁን ያሳያል። ብትበደሉ አይሻልምን? ብትታለሉስ አይሻልምን?
8
እናንተ ግን ራሳችሁ ትበድላላችሁ፤ ታታልላላችሁም፤ ያውም እኮ ወንድሞቻችሁን።
9
ዐመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደማይወርሱ አታውቁምን? በዚህ ነገር አትታለሉ፤ ሴሰኞች፣ ጣዖት አምላኪዎች፣ አመንዝሮች፣ ወንደቃዎች፣ ግብረ ሰዶማውያን፣
10
ወይም ሌቦች፣ ስግብግቦች፣ ሰካራሞች፣ ተሳዳቢዎችና ቀማኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።
11
ከእናንተ አንዳንዶቻችሁ እንደዚህ ነበራችሁ፤ አሁን ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስምና በአምላካችን መንፈስ ታጥባችኋል፤ ተቀድሳችኋል፤ ጸድቃችኋል።
12
“ሁሉ ነገር ተፈቅዶልኛል፤” ይሁን እንጂ ሁሉም ነገር አይጠቅምም፤ “ሁሉ ነገር ተፈቅዶልኛል፤” ይሁን እንጂ ምንም ነገር በእኔ ላይ አይሠለጥንም።
13
ደግሞም፣ “ምግብ ለሆድ ነው፤ ሆድም ለምግብ ነው፤” እግዚአብሔር ግን ሁለቱንም ያጠፋቸዋል። ሰውነት ለጌታ ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም፤ ጌታም ለሰውነት ነው።
14
እግዚአብሔር ጌታን ከሙታን እንዳስነሣው፣ እኛንም ደግሞ በኀይሉ ከሙታን ያስነሣናል።
15
ሰውነታችሁ የክርስቶስ የአካሉ ብልቶች እንደ ሆነ አታውቁምን? ታዲያ፣ የክርስቶስን ብልቶች ወስጄ ከዝሙት ዐዳሪ ሴት ብልቶች ጋር አንድ ላድርገውን? ከቶ አይገባም!
16
ወይስ ከዝሙት ዐዳሪ ጋር የሚተባበር ሰው ከእርሷ ጋር አንድ ሥጋ እንደሚሆን አታውቁምን? “ሁለቱ አንድ ሥጋ ይሆናሉ” ተብሏልና።
17
ነገር ግን ከጌታ ጋር የሚተባበር ከእርሱ ጋር አንድ መንፈስ ይሆናል።
18
ከዝሙት ሽሹ። ሰው የሚሠራው ኀጢአት ሁሉ ከአካሉ ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚፈጽም ግን በገዛ አካሉ ላይ ኀጢአት ይሠራል።
19
ለመሆኑ፣ ሰውነታችሁ በውስጣችሁ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? ይህም መንፈስ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት ነው። እናንተም የራሳችሁ አይደላችሁም፤
20
በዋጋ ተገዝታችኋልና፤ ስለዚህ በሰውነታችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።
← Chapter 5
Chapter 7 →