bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
1 Corinthians 11
1 Corinthians 11
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
እኔ የክርስቶስን ምሳሌ እንደምከተል እናንተም የእኔን ተከተሉ።
2
በሁሉም ነገር ስለምታስቡልኝና ከእኔ የተቀበላችሁትን ትምህርት አጥብቃችሁ ስለ ያዛችሁ አመሰግናችኋለሁ።
3
ነገር ግን ይህን እንድታውቁ እወድዳለሁ፤ የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ ነው፤ የሴትም ራስ ወንድ ነው፤ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር ነው።
4
ራሱን ተከናንቦ የሚጸልይ ወይም ትንቢት የሚናገር ማንኛውም ወንድ የእርሱን ራስ ያዋርዳል፤
5
ራሷን ሳትሸፍን የምትጸልይ ወይም ትንቢት የምትናገር ማንኛዋም ሴት የእርሷን ራስ ታዋርዳለች፤ ጠጕሯን እንደ ተላጨች ይቈጠራልና።
6
ሴት ራሷን የማትሸፍን ከሆነ፣ ጠጕሯን ትቈረጥ፤ ጠጕሯን መቈረጥ ወይም መላጨት የሚያሳፍር መስሎ ከታያት ግን ራሷን ትሸፈን።
7
ወንድ ራሱን መከናነብ የለበትም፤ ወንድ የእግዚአብሔር ምሳሌና ክብር ነውና፤ ሴት ግን የወንድ ክብር ናት፤
8
ምክንያቱም ሴት ከወንድ ተገኘች እንጂ ወንድ ከሴት አልተገኘም።
9
ደግሞም ሴት ለወንድ ተፈጠረች እንጂ ወንድ ለሴት አልተፈጠረም።
10
በዚህ ምክንያት፣ በመላእክትም ምክንያት፣ ሴት በሥልጣን ሥር መሆኗን የሚያሳይ ምልክት በራሷ ላይ ታድርግ።
11
በጌታ ዘንድ ግን ሴት ያለ ወንድ፣ ወንድም ያለ ሴት አይሆንም።
12
ሴት ከወንድ እንደ ተገኘች ሁሉ፣ ወንድም ከሴት ይወለዳልና፤ ነገር ግን የሁሉም መገኛ እግዚአብሔር ነው።
13
እስቲ እናንተ ፍረዱ፤ ሴት ራሷን ሳትሸፍን ወደ እግዚአብሔር መጸለይ ይገባታልን?
14
ወንድ ጠጕሩን ቢያስረዝም ነውር እንደሚሆንበት ተፈጥሮ እንኳ አያስተምራችሁምን?
15
ሴት ግን ጠጕሯን ብታስረዝም ክብሯ አይደለምን? ረዥም ጠጕር የተሰጣት መጐናጸፊያ እንዲሆናት ነውና።
16
እንግዲህ ማንም በዚህ ጕዳይ ላይ መከራከር ቢፈልግ፣ እኛም ሆንን የእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት ከዚህ የተለየ ልማድ የለንም።
17
ነገር ግን በምትሰበሰቡበት ጊዜ ለሚጐዳ እንጂ ለሚጠቅም ስላልሆነ፣ ይህን ትእዛዝ ስሰጥ እያመሰገንኋችሁ አይደለም።
18
ከሁሉ አስቀድሞ በቤተ ክርስቲያን በምትሰበሰቡበት ጊዜ በመካከላችሁ መለያየት እንዳለ ሰምቻለሁ፤ ይህም ሊሆን እንደሚችል በከፊል አምናለሁ።
19
ከእናንተ መካከል እውነተኞቹ ተለይተው ይታወቁ ዘንድ፣ ይህ መለያየት በመካከላችሁ መኖሩ የግድ ነው።
20
በምትሰበሰቡበት ጊዜ የምትበሉት የጌታን እራት አይደለም፤
21
በምትበሉበት ጊዜ አንዱ ሌላውን ሳይጠብቅ ምግቡን ይበላልና፤ አንዱ እየተራበ ሌላው ይሰክራል።
22
ለመሆኑ የምትበሉበትና የምትጠጡበት ቤት የላችሁምን? ወይስ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን በመናቅ፣ ምንም የሌላቸውን ታሳፍራላችሁን? እንግዲህ ምን ልበላችሁ? በዚህ ነገር ላመስግናችሁን? ፈጽሞ አላመሰግናችሁም።
23
እኔ ከጌታ የተቀበልሁትን ለእናንተ አስተላልፌአለሁና፤ ጌታ ኢየሱስ ዐልፎ በተሰጠባት ሌሊት እንጀራን አንሥቶ
24
ከባረከ በኋላ ቈርሶ፣ “ይህ ስለ እናንተ የሚሆን ሥጋዬ ነው፤ ለመታሰቢያዬም አድርጉት” አለ።
25
እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ፣ “ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው፤ ስለዚህ ከጽዋው በምትጠጡበት ጊዜ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” አለ።
26
ይህን እንጀራ በምትበሉበት ጊዜ፣ ይህንም ጽዋ በምትጠጡበት ጊዜ ሁሉ ጌታ እስከሚመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁ።
27
እንግዲህ ማንም ሳይገባው፣ ይህን እንጀራ ቢበላ ወይም የጌታን ጽዋ ቢጠጣ፣ የጌታ ሥጋና ደም ባለ ዕዳ ይሆናል።
28
ማንም ሰው ከዚህ እንጀራ ከመብላቱና ከዚህ ጽዋ ከመጠጣቱ በፊት፣ ራሱን ይመርምር፤
29
ምክንያቱም ማንም የጌታን ሥጋ ሳይገባው ቢበላና ቢጠጣ ፍርድ የሚያመጣበትን ይበላል፤ ይጠጣልም።
30
ከእናንተ መካከል ብዙዎች የደከሙትና የታመሙት፣ አንዳንዶችም ያንቀላፉት በዚህ ምክንያት ነው።
31
ራሳችንን ብንመረምር ግን ባልተፈረደብን ነበር።
32
ነገር ግን ጌታ በሚፈርድብን ጊዜ እንገሠጻለን፤ ይኸውም ከዓለም ጋር አብረን እንዳንኰነን ነው።
33
ስለዚህ ወንድሞቼ ሆይ፤ ለመብላት በምትሰበሰቡበት ጊዜ እርስ በርሳችሁ ተጠባበቁ።
34
በምትሰበሰቡበት ጊዜ ለፍርድ እንዳይሆንባችሁ፣ ማንም የራበው ሰው ቢኖር በቤቱ ይብላ። ስለ ቀረው ነገር ደግሞ በምመጣበት ጊዜ እደነግጋለሁ።
← Chapter 10
Chapter 12 →