bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
1 Chronicles 28
1 Chronicles 28
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ዳዊት በኢየሩሳሌም እንዲሰበሰቡ የነገዱን የጦር አለቆች፣ ንጉሡን የሚያገለግሉትን የከፍለ ጦር አዛዦች፣ የሻለቆቹን፣ የመቶ አለቆቹን፣ የንጉሡና የልጆቹ ንብረትና ከብት ሁሉ ኀላፊ የሆኑትን፣ እንዲሁም የቤተ መንግሥቱን ሹማምት፣ ኀያላንና ጀግና ተዋጊዎቹን፣ በአጠቃላይ የእስራኤልን ሹማምት ሁሉ ጠራ።
2
ከዚያም ንጉሥ ዳዊት በእግሩ ቆሞ እንዲህ አላቸው፤ “ወንድሞቼና ወገኖቼ ሆይ፤ እስቲ አድምጡኝ፤ ለእግዚአብሔር ለቃል ኪዳኑ ታቦት ማደሪያና ለአምላካችን እግር ማረፊያ የሚሆን ቤት ለመሥራት ዐስቤ ዕቅድ አውጥቼ ነበር።
3
እግዚአብሔር ግን እንዲህ አለኝ፤ ‘ጦረኛ ሰው ስለ ሆንህና ደምም ስላፈሰስህ፣ አንተ ለስሜ ቤት አትሠራም።’
4
“ነገር ግን የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ለዘላለም እንድነግሥ ከቤተ ሰቤ ሁሉ እኔን መረጠ፤ መሪ እንዲሆንም ይሁዳን መረጠ፤ ከይሁዳም ቤት የእኔን ቤተ ሰብ መረጠ፤ ከአባቴ ልጆች መካከል ደግሞ በመላው እስራኤል ላይ እንድነግሥ ፈቃዱ ሆነ።
5
እግዚአብሔር ብዙ ልጆች ሰጥቶኛል፤ ከወንዶቹ ልጆቼ ሁሉ በእግዚአብሔር መንግሥት ዙፋን ላይ ተቀምጦ በእስራኤል ሁሉ ላይ እንዲነግሥ ደግሞ ልጄን ሰሎሞንን መርጦታል።
6
እንዲህም አለኝ፤ ‘ቤቴንና አደባባዮቼን የሚሠራልኝ ልጅህ ሰሎሞን ነው፤ ምክንያቱም ልጄ እንዲሆን መርጬዋለሁ፤ እኔም አባት እሆነዋለሁ።
7
አሁን እንደሚያደርገው ሁሉ፣ ትእዛዞቼንና ሕጎቼን ምንጊዜም ሳያወላውል የሚፈጽም ከሆነ፣ መንግሥቱን ለዘላለም አጸናታለሁ’።
8
“እንግዲህ አሁንም ይህችን መልካሚቱን ምድር እንድትወርሱና ለልጆቻችሁም የዘላለም ርስት አድርጋችሁ እንድታወርሷቸው፣ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ሁሉ በጥንቃቄ እንድታከብሩ በእስራኤል ሁሉ ፊት፣ በእግዚአብሔር ጉባኤና እግዚአብሔርም እየሰማ አዝዛችኋለሁ።
9
“አንተም ልጄ ሰሎሞን ሆይ፤ እግዚአብሔር ልብን ሁሉ ስለሚመረምርና ሐሳብን ሁሉ ስለሚያውቅ፣ የአባትህን አምላክ ዕወቅ፤ በፍጹም ልብና በበጎ ፈቃድ አገልግለው። ከፈለግኸው ታገኘዋለህ፤ ከተውኸው ግን እርሱም ለዘላለም ይተውሃል።
10
ለመቅደስ የሚሆን ቤት እንድትሠራ እግዚአብሔር የመረጠህ መሆኑን አሁንም ዐስብ፤ በርትተህም ሥራ።”
11
ከዚያም ዳዊት የቤተ መቅደሱን መመላለሻ፣ የሕንጻውን፣ የዕቃ ቤቶቹን፣ የፎቁንና የውስጥ ክፍሎቹን እንዲሁም የማስተስረያውን ቦታ ንድፍ ለልጁ ለሰሎሞን ሰጠው።
12
ደግሞም መንፈስ ቅዱስ በልቡ ያሳደረውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አደባባይ፣ በዙሪያው ያሉትን ክፍሎች ሁሉ፣ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ዕቃ ቤቶችና የንዋየ ቅድሳቱን ግምጃ ቤቶች ንድፍ ሁሉ ሰጠው፤
13
እንዲሁም የካህናቱንና የሌዋውያኑን አመዳደብ፣ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አገልግሎት ሥራና ለአገልግሎቱ ስለሚጠቀምባቸው ዕቃዎች ሁሉ መመሪያ ሰጠው።
14
ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚውሉትን የወርቅ ዕቃዎች ሁሉ መጠን፣ ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚውሉትን የብር ዕቃዎች ሁሉ መጠን አሳወቀው፤
15
እንደየመቅረዙ አገልግሎት ዐይነት ለወርቁ መቅረዞችና ለቀንዲሎቻቸው የሚሆነውን የእያንዳንዳቸውን የወርቅ መጠን፣ ለብሩ መቅረዞችና ለቀንዲሎቻቸው የሚያስፈልገውን የእያንዳንዳቸውን የብር መጠን፣
16
ለእያንዳንዱ፣ ገጸ ኅብስት ጠረጴዛ የሚያስፈልገውን የወርቅ መጠን፣ ለእያንዳንዱም የብር ጠረጴዛ የሚያስፈልገውን የብር መጠን፣
17
ለሹካዎቹ፣ ለጐድጓዳ ሳሕኖቹ፣ ለማንቈርቈርያዎቹ የሚያስፈልገውን ንጹሕ የወርቅ መጠን፣ ለእያንዳንዱ የብር ሳሕን የሚያስፈልገውን የብር መጠን፣
18
ለዕጣኑ መሠዊያ የሚሆነውን የጠራ ወርቅ መጠን እንዲሁም ክንፎቻቸውን ዘርግተው የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት የሚሸፍኑትን ከወርቅ የተሠሩትን የኪሩቤል ሠረገሎች ንድፍ ሰጠው።
19
ዳዊትም፣ “ይህ ሁሉ፣ በእኔ ላይ ባለው በእግዚአብሔር እጅ በጽሑፍ ተገለጠልኝ፤ የንድፉንም ዝርዝር እንድረዳ ማስተዋልን ሰጠኝ” አለ።
20
ደግሞም ዳዊት ልጁን ሰሎሞንን እንዲህ አለው፤ “እንግዲህ በርታ፤ ጠንክር፤ ሥራውንም ጀምር። አትፍራ፤ ተስፋም አትቍረጥ፤ እግዚአብሔር አምላኬ ከአንተ ጋር ነውና፤ እርሱም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አገልግሎት ሥራ እስኪፈጸም ድረስ አይተውህም፤ አይጥልህም።
21
ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሥራ ሁሉ የሚያስፈልጉት ካህናትና ሌዋውያን ምድብም ዝግጁ ነው። በሁሉም የእጅ ሙያ የሠለጠኑ ፈቃደኛ ሰዎች በሥራው ሁሉ ይረዱሃል። ሹማምቱና ሕዝቡ ሁሉ ትእዛዝህን ይፈጽማሉ።”
← Chapter 27
Chapter 29 →