bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic Catholic Version (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)) No Year
/
Psalms 119
Psalms 119
Amharic Catholic Version (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)) No Year
1
በመንገዳቸው እንከን የሌለባቸው፥ በጌታም ሕግ የሚመላለሱ ምስጉኖች ናቸው።
2
ሕጉን የሚጠብቁ፥ በፍጹም ልብ የሚሹት ምስጉኖች ናቸው፥
3
ዓመፅንም አያደርጉም፥ በመንገዶቹም ይሄዳሉ።
4
ሕጎችህን በሚገባ እንጠብቅ ዘንድ አንተ አዘዝህ።
5
ደንቦችህን ለመጠበቅ መንገዶቼ ምነው በቀኑ።
6
ትእዛዞችህንም ሁሉ ስመለከት በዚያን ጊዜ አላፍርምና።
7
አቤቱ፥ ትክክለኛ ፍርድህን ስማር በቅን ልብ አመሰግንሃለሁ።
8
ሥርዓትህን እጠብቃለሁ፥ በፍጹም አትጣለኝ።
9
ጎልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል? ቃልህን በመጠበቅ ነው።
10
በፍጹም ልቤ ፈለግሁህ፥ ከትእዛዝህ አታርቀኝ።
11
አንተን እንዳልበድል፥ ቃልህን በልቤ ሰወርሁ።
12
አቤቱ፥ አንተ ቡሩክ ነህ፥ ደንቦችህን አስተምረኝ።
13
ከአፍህ የሚወጡትን ፍርዶች ሁሉ በከንፈሮቼ ደገምኳቸው።
14
በብልጽግና እንደሚደሰቱ ሁሉ በሕጎችህ መንገድ ደስ አለኝ።
15
ደንቦችህን አሰላስላለሁ፥ መንገዶችህንም እመለከታለሁ።
16
በድንጋጌዎችህ ደስ ይለኛል፥ ቃልህንም አልረሳም።
17
ለአገስልጋይህ መልካም አድርግለት፤ ሕያው እንድሆን፥ ቃልህንም እንድጠብቅ።
18
ዐይኖቼን ክፈት፥ ከሕግህም ተኣምራትህን አያለሁ።
19
እኔ በምድር እንግዳ ነኝ፥ ትእዛዛትህን ከእኔ አትሰውር።
20
ፍርዶችህን ሁልጊዜ በመፈለግ ነፍሴ በናፍቆት ደቀቀች።
21
ከትእዛዛትህ የሚያፈነግጡተን ትዕቢተኞችንና ርጉማንን ገሠጽህ።
22
ሕግህን ጠብቄአለሁና። ስድብንና ነውርን ከእኔ አርቅ።
23
መስፍኖች ደግሞ ተቀምጠው እኔን አሙኝ፥ አገልጋይህ ግን ሕግህን ያሰላስል ነበር።
24
ሕግህም ተድላዬ ነው፥ ደንቦችህም አማካሪዎቼ ናቸው።
25
ነፍሴ ወደ አፈር ተጠጋች፥ እንደ ቃልህ ሕያው አድርገኝ።
26
መንገዶቼን ዘረዘርሁ፥ ሰማኸኝም፥ ደንቦችህን አስተምረኝ።
27
የድንጋጌዎችህን መንገድ እንዳስተውል አድርገኝ፥ ተኣምራትህንም አሰላስላለሁ።
28
ከኀዘን የተነሣ ነፍሴ በዕንባ ተዋጠች፥ እንደ ቃልህ አጠንክረኝ።
29
የሐሰትን መንገድ ከእኔ አርቅ፥ የሕግህንም ጸጋ ስጠኝ፥
30
የእውነትህን መንገድ መረጥሁ፥ ፍርድህንም አልረሳሁም።
31
አቤቱ፥ ሕግህን ተጠጋሁ፥ አታሳፍረኝ።
32
ልቤን ባሰፋኸው ጊዜ፥ በትእዛዞችህ መንገድ ሮጥሁ።
33
አቤቱ፥ የደንቦችህን መንገድ አስተምረኝ፥ ለትሩፋትም እጠብቀዋለሁ።
34
እንዳስተውል አድርገኝ፥ ሕግህንም እንድጠብቅ፥ በፍጹም ልቤም እጠብቀዋለሁ።
35
እርሷን ወድጃለሁና የትእዛዝህን መንገድ ምራኝ።
36
ልቤን ወደ ምስክርህ አዘንብል፥ ወደ ስስትም አይሁን።
37
ከንቱ ነገርን እንዳያዩ ዐይኖቼን መልስ፥ በመንገድህ ሕያው አድርገኝ።
38
እንዲፈራህ ባርያህን በቃልህ አጽና።
39
ፍርድህ መልካም ናትና የምፈራውን ስድብ ከእኔ አርቅ።
40
እነሆ፥ ትእዛዝህን ናፈቅሁ፥ በጽድቅህ ሕያው አድርገኝ።
41
አቤቱ፥ እንደ ቃልህ፥ ምሕረትህና መድኃኒትህ ይምጡልኝ።
42
በቃልህ ታምኛለሁና ለሚሰድቡኝ በነገር እመልስላቸዋለሁ።
43
በፍርድህም ታምኛለሁና የእውነትን ቃል ከአፌ ፈጽመህ አታርቅ።
44
ለዘለዓለም ዓለም ሁልጊዜ ሕግህን እጠብቃለሁ።
45
ትእዛዛትህንም ፈልጌአለሁና አስፍቼ እሄዳለሁ።
46
በነገሥታት ፊት ምስክርህን እናገራለሁ፥ አላፍርምም፥
47
እጅግም በወደድኋቸው በትእዛዛትህ ደስ ይለኛል።
48
እጆቼንም ወደ ወደድኋቸው ወደ ትእዛዛትህ አነሣለሁ፥ ሥርዓትህንም አሰላስላለሁ።
49
ለባርያህ የሰጠኸውን የተስፋ ቃልህን አስብ።
50
ቃልህ ሕያው አድርጎኛልና ይህች በመከራዬ ደስ አሰኘችኝ።
51
ትዕቢተኞች እጅግ ዐመፁ፥ እኔ ግን ከሕግህ አልራቅሁም።
52
ከጥንት የነበረውን ፍርድህን አሰብሁ፥ አቤቱ፥ ተጽናናሁም።
53
ሕግህን ከተዉ ከኃጢአተኞች የተነሣ ኀዘን ያዘኝ።
54
በእንግድነቴ አገር ሥርዓትህ መዝሙር ሆነችኝ።
55
አቤቱ፥ በሌሊት ስምህን አሰብሁ፥ ሕግህንም ጠበቅሁ።
56
ትእዛዛትህንም ፈልጌአለሁና ይህች ሆነችልኝ።
57
ጌታ ድርሻዬ ነው፥ ቃልህን እጠብቃለሁ አልሁ።
58
በፍጹም ልቤ ወደ ፊትህ ተማለልሁ፥ እንደ ቃልህ ማረኝ።
59
ስለ መንገዶችህ አሰብሁ፥ እግሬንም ወደ ምስክሮችህ መለስሁ።
60
ትእዛዝህን ለመጠበቅ ጨከንሁ አልዘገየሁምም።
61
የኀጥኣን ገመዶች ተተበተቡብኝ፥ ሕግህን ግን አልረሳሁም።
62
ስለ ጽድቅህ ፍርድ፥ በእኩለ ሌሊት አመሰግንህ ዘንድ እነሣለሁ።
63
እኔ ለሚፈሩህ ሁሉ፥ ትእዛዝህንም ለሚጠብቁ ባልንጀራ ነኝ።
64
አቤቱ፥ ምሕረትህ በምድር ሁሉ ሞላች፥ ሥርዓትህን አስተምረኝ።
65
አቤቱ፥ እንደ ቃልህ ለባርያህ መልካም አደረግህ።
66
በትእዛዛትህ ታምኛለሁና መልካም ምክርና እውቀትን አስተምረኝ።
67
በፊት ስቼ ከመንገድህ ርቄ ነበር፥ አሁን ግን ቃልህን ጠበቅሁ።
68
አቤቱ፥ አንተ ቸር ነህ፥ በቸርነትህም ሥርዓትህን አስተምረኝ።
69
የትዕቢተኞች ዓመጽ በላዬ በዛ፥ እኔ ግን በፍጹም ልቤ ትእዛዛትህን እፈልጋለሁ።
70
ልባቸው እንደ ወተት ረጋ፥ እኔ ግን በሕግህ ደስ ይለኛል።
71
ሥርዓትህን እማር ዘንድ ያስጨነቅኸኝ መልካም ሆነልኝ።
72
ከአእላፋት ወርቅና ብር ይልቅ የአፍህ ሕግ ይሻለኛል። ዮድ።
73
እጆችህ ሠሩኝ አበጃጁኝም፥ እንዳስተውል አድርገኝ፥ ትእዛዛትህንም እማራለሁ።
74
በቃልህ ታምኛለሁና የሚፈሩህ እኔን አይተው ደስ ይላቸዋል።
75
አቤቱ፥ ፍርድህ ጽድቅ እንደ ሆነች፥ በእውነትህም እንዳስቸገርኸኝ አወቅሁ።
76
ምሕረትህ ለመጽናናቴ ትሁነኝ፥ እንደ ቃልህም ለባርያህ ይሁነው።
77
ሕግህ ተድላዬ ናትና ቸርነትህ ትምጣልኝ፥ በሕይወትም ልኑር።
78
ትዕቢተኞች በዓመፅ ጠምመውብኛልና ይፈሩ፥ እኔ ግን ትእዛዝህን አሰላስላለሁ።
79
የሚፈሩህና ምስክሮችህን የሚያውቁ ወደ እኔ ይመለሱ።
80
እንዳላፍር ልቤ በሥርዓትህ የቀና ይሁን።
81
ነፍሴ መድኃኒትህን ናፈቀች፥ በቃልህም ታመንሁ።
82
መቼ ታጽናናኛለህ እያልሁ ዐይኖቼ ስለ ቃልህ ፈዘዙ።
83
በጢስ ውስጥ እንዳለ አቁማዳ ሆኛለሁና፥ ሥርዓትህን ግን አልረሳሁም።
84
የባርያህ ዘመኖች ስንት ናቸው? በሚያሳድዱኝስ ላይ መቼ ትፈርድልኛለህ?
85
ኃጢአተኞች ጉድጓድ ቆፈሩልኝ፥ አቤቱ፥ እንደ ሕግህ ግን አይደለም።
86
ትእዛዛትህ ሁሉ እውነት ናቸው፥ በዓመፅ አሳድደውኛል፥ እርዳኝ።
87
ከምድር ሊያጠፉኝ ጥቂት ቀርቶአቸው ነበር፥ እኔ ግን ትእዛዛትህን አልተውሁም።
88
እንደ ምሕረትህ ሕያው አድርገኝ፥ የአፍህንም ምስክር እጠብቃለሁ።
89
አቤቱ፥ ቃልህ በሰማይ ለዘለዓለም ይኖራል።
90
እውነትህ ለልጅ ልጅ ናት፥ ምድርን መሠረትሃት እርሷም ትኖራለች።
91
ሁሉም ባርያዎችህ ናቸውና ቀኑ በትእዛዝህ ይኖራል።
92
ሕግህ ተድላዬ ባይሆን፥ ቀድሞ በጉስቁልናዬ በጠፋሁ ነበር።
93
በእርሱ ሕያው አድርገኸኛልና ፍርድህን ለዘለዓለም አልረሳም።
94
እኔ የአንተ ነኝ፥ ፍርድህን ፈልጌአለሁና አድነኝ።
95
ኃጢአተኞች ያጠፉኝ ዘንድ ጠበቁኝ፥ ምስክርህን ግን መረመርሁ።
96
የሥራን ሁሉ ፍጻሜ አየሁ፥ ትእዛዝህ ግን እጅግ ሰፊ ነው።
97
አቤቱ፥ ሕግህን እንደምን እጅግ ወደድሁ! ቀኑን ሁሉ እርሱ ትዝታዬ ነው።
98
ለዘለዓለም ለእኔ ነውና ትእዛዝህ ከጠላቶቼ ይልቅ አስተዋይ አደረገኝ።
99
ምስክርህ ትዝታዬ ነውና ካስተማሩኝ ሁሉ ይልቅ አስተዋልሁ።
100
ትእዛዝህን ፈልጌአለሁና ከሽማግሌዎች ይልቅ አስተዋልሁ።
101
ቃልህን እጠብቅ ዘንድ ከክፉ መንገድ ሁሉ እግሬን ከለከልሁ።
102
አስተምረኸኛልና ከፍርድህ አልራቅሁም።
103
ቃልህ ለጉሮሮዬ ጣፋጭ ነው፥ ከማርና ከወለላ ይልቅ ለአፌ ጣፈጠኝ።
104
ከትእዛዝህ የተነሣ አስተዋልሁ፥ ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ጠላሁ።
105
ሕግህ ለእግሬ መብራት፥ ለመንገዴ ብርሃን ነው።
106
የጽድቅህን ፍርድ እጠብቅ ዘንድ ማልሁ፥ አጸናሁም።
107
እጅግ ተቸገርሁ፥ አቤቱ፥ እንደ ቃልህ ሕያው አድርገኝ።
108
አቤቱ፥ ከአፌ የሚወጣውን ቃል ውደድ፥ ፍርድህንም አስተምረኝ።
109
ነፍሴ ሁልጊዜ በእጅህ ውስጥ ናት፥ ሕግህን ግን አልረሳሁም።
110
ኃጢአተኞች ወጥመድን ዘረጉብኝ፥ ከትእዛዝህ ግን አልሳትሁም።
111
የልቤ ደስታ ነውና ምስክርህን ለዘለዓለም ወረስሁ።
112
ለዘለዓለም ለፍጻሜውም ትእዛዝህን አደርግ ዘንድ ልቤን አዘነበልሁ።
113
ዓመፀኞችን ጠላሁ፥ ሕግን ግን ወደድሁ።
114
አንተ ረዳቴና መጠጊያዬ ነህ፥ በቃልህም ተማመንሁ።
115
እናንተ ኃጢአተኞች፥ ከእኔ ራቁ፥ የአምላኬንም ትእዛዝ ልፈልግ።
116
እንደ ቃልህ ደግፈኝ፥ ሕያውም እሆናለሁ፥ ከተስፋዬም አልፈር።
117
እርዳኝ እድናለሁም፥ ሁልጊዜም ሥርዓትህን እመረምራለሁ።
118
ምኞታቸው ዓመፃ ነውና ከሥርዓትህ የሚርቁትን ሁሉ አጐሳቈልሃቸው።
119
የምድርን ኃጢአተኞች ሁሉ እንደ ርኩሰት አጠፋሃቸው፥ ስለዚህ ምስክርህን ወደድሁ።
120
ሥጋዬ አንተን ከመፍራት የተነሣ ደነገጠ፥ ከፍርድህ የተነሣ ፈርቻለሁ።
121
ፍርድንና ጽድቅን ሠራሁ፥ ለሚያስጨንቁኝ አሳልፈህ አትስጠኝ።
122
ባርያህን በመልካም ጠብቀው፥ ትዕቢተኞችም አይጋፉኝ።
123
ዐይኖቼ ለማዳንህ፥ ለጽድቅህም ቃል ፈዘዙ።
124
ለባርያህ እንደ ምሕረትህ አድርግ፥ ሥርዓትህንም አስተምረኝ።
125
እኔ ባርያህ ነኝ፥ እንዳስተውል አድርገኝ፥ ምስክርህንም አውቃለሁ።
126
ለጌታ የሥራ ጊዜ ነው፥ ሕግህንም ሻሩት።
127
ስለዚህ ከወርቅና ከዕንቁ ይልቅ ትእዛዝህን ወደድሁ።
128
ስለዚህ ወደ ትእዛዝህ ሁሉ አቀናሁ፥ የዓመፅንም መንገድ ሁሉ ጠላሁ።
129
ምስክሮችህ ድንቆች ናቸው፥ ስለዚህ ነፍሴ ፈለገቻቸው።
130
የቃልህ ፍቺ ያበራል፥ ሕፃናትንም አስተዋዮች ያደርጋል።
131
አፌን ከፈትሁ፥ አለከለክሁም፥ ወደ ትእዛዝህ ናፍቄአለሁና።
132
ስምህን ለሚወድዱ እንደምታደርገው ፍርድ፥ ወደ እኔ ተመልከት ማረኝም።
133
አካሄዴን እንደ ቃልህ አቅና፥ ኃጢአትም ሁሉ አይግዛኝ።
134
ከሰው ግፍ አድነኝ፥ ትእዛዝህንም እጠብቃለሁ።
135
በባርያህ ላይ ፊትህን አብራ፥ ሥርዓትህንም አስተምረኝ።
136
ሕግህን አልጠበቅሁምና የውኃ ፈሳሽ ከዐይኖቼ ፈሰሰ።
137
አቤቱ፥ አንተ ጻድቅ ነህ፥ ፍርድህም ቅን ነው።
138
ምስክርህን በጽድቅ አዘዝህ፥ እጅግም ቅን ነው።
139
ጠላቶቼ ቃልህን ረስተዋልና የቤትህ ቅንዓት አቀለጠኝ።
140
ቃልህ እጅግ የነጠረ ነው፥ ባርያህም ወደደው።
141
እኔ ታናሽና የተናቅሁ ነኝ፥ ትእዛዛትህን ግን አልረሳሁም።
142
ጽድቅህ የዘለዓለም ጽድቅ ነው፥ ቃልህም እውነት ነው።
143
መከራና ችግር አገኙኝ፥ ትእዛዛትህ ግን ተድላዬ ናቸው።
144
ምስክርህ ለዘለዓለም ጽድቅ ነው፥ እንዳስተውል አድርገኝ፥ በሕይወትም አኑረኝ።
145
በፍጹም ልቤ ጮኽሁ፥ አቤቱ፥ ስማኝ፥ ሥርዓትህን እፈልጋለሁ።
146
ወደ አንተ ጮኽሁ፥ አድነኝ፥ ምስክርህንም እጠብቃለሁ።
147
ማለዳ ጮኽሁ፥ ቃልህንም ተስፋ አድርጌአለሁ።
148
ቃልህን አስብ ዘንድ ዐይኖቼ ለመማለድ ቀደሙ።
149
አቤቱ፥ እንደ ቸርነትህ ድምፄን ስማ፥ እንደ ፍርድህ ሕያው አድርገኝ።
150
በዓመፃ የሚያሳድዱኝ ቀረቡ፥ ከሕግህም ራቁ።
151
አቤቱ፥ አንተ ቅርብ ነህ፥ መንገዶችህም ሁሉ ቅኖች ናቸው።
152
ከዘለዓለም እንደ መሠረትኸው ከቀድሞ ጀምሮ ከምስክርህ የተነሣ አወቅሁ።
153
ሕግህን አልረሳሁምና ችግሬን ተመልከት አድነኝም።
154
ፍርዴን ፍረድ አድነኝም፥ ስለ ቃልህ ሕያው አድርገኝ።
155
መድኃኒት ከኀጥኣን ሩቅ ነው፥ ሥርዓትህን አልፈለጉምና።
156
አቤቱ፥ ቸርነትህ እጅግ ብዙ ነው፥ እንደ ፍርድህ ሕያው አድርገኝ።
157
ያሳደዱኝና ያስጨነቁኝ ብዙዎች ናቸው፥ ከምስክር ግን ፈቀቅ አላልሁም።
158
ቃልህን አልጠበቁምና ሰነፎችን አይቼ አዘንሁ።
159
ትእዛዝህን እንደ ወደድሁ ተመልከት፥ አቤቱ፥ በምሕረትህ ሕያው አድርገኝ።
160
የቃልህ መጀመሪያ እውነት ነው፥ የጽድቅህም ፍርድ ሁሉ ለዘለዓለም ነው።
161
ገዢዎች በከንቱ አሳደዱኝ፥ ከቃልህ የተነሣ ግን ልቤ ደነገጠብኝ።
162
ብዙ ምርኮ እንዳገኘ በቃልህ ደስ አለኝ።
163
ዓመፃን ጠላሁ ተጸየፍሁም፥ ሕግህን ግን ወደድሁ።
164
ስለ ጽድቅህ ፍርድ ሰባት ጊዜ በቀን አመሰግንሃለሁ።
165
ሕግህን ለሚወድዱ ብዙ ሰላም ነው፥ ዕንቅፋትም የለባቸውም።
166
አቤቱ፥ ማዳንህን ተስፋ አደርግሁ፥ ትእዛዛትህንም ጠበቅሁ።
167
ነፍሴ ምስክርህን ጠበቀች እጅግም ወደደችው።
168
መንገዶቼ ሁሉ በፊትህ ናቸውና ትእዛዝህንና ምስክርህን ጠበቅሁ።
169
አቤቱ፥ ጸሎቴ ወደ ፊትህ ትቅረብ፥ እንደ ቃልህም አስተዋይ አድርገኝ።
170
ልመናዬ ወደ ፊትህ ትድረስ፥ እንደ ቃልህ አድነኝ።
171
ሥርዓትህን አስተምረኸኛልና ከንፈሮቼ ምስጋናን አወጡ።
172
ትእዛዛትህ ሁሉ ጽድቅ ናቸውና አንደበቴ ቃልህን ተናገረ።
173
ትእዛዛትህን መርጫለሁና እጅህ የሚያድነኝ ይሁን።
174
አቤቱ፥ ማዳንህን ናፈቅሁ፥ ሕግህም ተድላዬ ነው።
175
ነፍሴ ትኑርልኝ ታመሰግንህማለች፥ ፍርድህም ይርዳኝ።
176
እንደ ጠፋ በግ ተቅበዘበዝሁ፥ ትእዛዛትህን አልረሳሁምና ባርያህን ፈልገው።
← Chapter 118
Chapter 120 →