bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic Catholic Version (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)) No Year
/
Luke 10
Luke 10
Amharic Catholic Version (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)) No Year
1
ከዚህም በኋላ ጌታ ሌሎች ሰባ ሁለት ሰዎችን መረጠ፤ ሁለት ሁለትም አድርጎ ራሱ ሊሄድበት ወደአሰበው ከተማና ስፍራ ሁሉ አስቀድሞ ላካቸው።
2
እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “መከሩ ብዙ ነው፤ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ ስለዚህ የመከሩን ጌታ ለመከሩ ሠራተኞችን እንዲልክ ለምኑት።
3
እንግዲህ ሂዱ፤ እነሆ፥ እንደ በጎች በተኩላዎች መካከል እልካችኋለሁ።
4
ቦርሳም ከረጢትም ጫማም አትያዙ፤ በመንገድ ላይ ለማንም ሰላምታን አትስጡ።
5
ወደምትገቡበትም ቤት ሁሉ አስቀድማችሁ፦ ‘ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን፤’ በሉ።
6
በዚያም የሰላም ልጅ ቢኖር፥ ሰላማችሁ በእርሱ ላይ ያድርበታል፤ ካልሆነ ግን ይመለስላችኋል።
7
ለሠራተኛ ደሞዙ ይገባዋልና እነርሱ የሚሰጡአችሁን እየበላችሁና እየጠጣችሁ በዚያው ቤት ተቀመጡ። ከቤት ወደ ቤት አትዘዋወሩ።
8
ወደምትገቡባትም ከተማ ሁሉ ቢቀበሉአችሁ፥ የሚያቀርቡላችሁን ብሉ፤
9
በእርሷም ያሉትን ሕሙማንን ፈውሱና፦ ‘የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ቀርቦአል፤’ በሉአቸው።
10
ነገር ግን ወደምትገቡባት ከተማ ሁሉ ባይቀበሉአችሁ፥ ወደ አደባባዮቹዋ ወጥታችሁ እንዲህ በሉ፦
11
‘ከከተማችሁም በእግሮቻችን ላይ የተጣበቀብንን ትቢያ ሳይቀር እናንተን በመቃወም እናራግፋለን፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርቦአል፥ ይህን እወቁ።’
12
በዚያን ቀን ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶም ይቀልላታል እላችኋለሁ።
13
“ወዮልሽ ኮራዚን! ወዮልሽ ቤተሳይዳ! በእናንተ የተደረጉት ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርገው ቢሆን ኖሮ፥ ማቅ ለብሰው በአመድ ላይም ተቀምጠው፥ ገና ድሮ፥ ንስሐ በገቡ ነበር።
14
ነገር ግን በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል።
15
አንቺም ቅፍርናሆም፥ እስከ ሰማይ ከፍ የምትደረጊ ይመስልሻልን? ወደ ሲኦል ትወርጃለሽ።
16
“የሚሰማችሁ እኔን ይሰማል፤ እናንተንም የማይቀበል እኔን አይቀበልም፤ እኔንም የማይቀበል የላከኝን አይቀበልም።”
17
ሰባዎቹም ሰዎች በደስታ ተመልሰው፦ “ጌታ ሆይ! አጋንንት እንኳ በስምህ ተገዝተውልናል፤” አሉት።
18
ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ሰይጣንን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁት።
19
እነሆ፥ እባቡንና ጊንጡን እንድትረግጡ፥ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፤ የሚጐዳችሁም ምንም ነገር የለም።
20
ነገር ግን መናፍስት ስለ ተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ፤ ይልቁንም ስማችሁ በሰማያት ሰለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ።”
21
በዚያን ሰዓት ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ሐሴት አድርጎ እንዲህ አለ፦ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ! ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጽክላቸው አመሰግንሃለሁ፤ አዎን አባት ሆይ! መልካም ፈቃድህ በፊትህ እንዲህ ሆኖአልና።
22
ሁሉ ነገር ከአባቴ ተሰጥቶኛል፤ ወልድንም ማን እንደሆነ ከአብ በቀር ማንም የሚያውቅ የለም፤ አብንም ማን እንደሆነ ከወልድ በቀር ወልድም በፈቃዱ ከሚገልጥለት ሰው በቀር ማንም የሚያውቅ የለም።”
23
ደቀ መዛሙርቱም ለብቻቸው ሳሉ ወደ እነርሱ ዘወር ብሎ እንዲህ አላቸው፦ “የምታዩትን የሚያዩ ዐይኖች ብፁዓን ናቸው።
24
እላችኋለሁና፥ እናንተ የምታዩትን ብዙዎች ነቢያትና ነገሥታት ሊያዩ ወደዱ አላዩምም፤ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ወደዱ አልሰሙምም።”
25
እነሆም፥ አንድ ሕግ አዋቂ ተነሥቶ ሊፈትነው እንዲህ አለ፦ “መምህር ሆይ! የዘለዓለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ?”
26
እርሱም፦ “በሕግ ምን ተጽፎአል? እንዴትስ ታነበዋለህ?” አለው።
27
እርሱም መልሶ፦ “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም ኃይልህም በፍጹም አሳብህም ውደድ፤ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ፤” አለው።
28
ኢየሱስም፦ “በትክክል መልሰሃል፤ ይህን አድርግ በሕይወትም ትኖራለህ፤” አለው።
29
እርሱ ግን ራሱን ሊያጸድቅ ወድዶ ኢየሱስን፦ “ባልንጀራዬስ ማን ነው?” አለው።
30
ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፦ “አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ፤ በወንበዴዎችም እጅ ወደቀ፤ እነርሱም ደግሞ ገፈፉት፤ ደበደቡትም፤ በሕይወትና በሞት መካከልም ትተውት ሄዱ።
31
እንደ አጋጣሚም አንድ ካህን በዚያ መንገድ ወረደ፤ አይቶትም ገለል ብሎ አለፈ።
32
እንዲሁም ደግሞ አንድ ሌዋዊ ወደዚያ ስፍራ መጣና አይቶት ገለል ብሎ አለፈ።
33
አንድ ሳምራዊ ግን በጉዞ ላይ ሳለ እርሱ ወደ ነበረበት መጣ አይቶትም አዘነለት፤
34
ቀርቦም ዘይትና የወይን ጠጅ በቁስሎቹ ላይ አፍስሶ አሰራቸው፤ በራሱ አህያም ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች ማደሪያ ወሰደው፤ ተንከባከበውም።
35
በማግሥቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለእንግዳ ማደሪያው ባለቤት ሰጠና፦ ‘ተንከባከበው፤ ከዚህም በላይ የምታወጣውን ወጪ ሁሉ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ፤’ አለው።
36
እንግዲህ ከነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ሰው ባልንጀራ የሆነው ማንኛው ይመስልሃል?”
37
እርሱም፦ “ምሕረት ያደረገለት፤” አለ። ኢየሱስም፦ “ሂድ አንተም እንዲሁ አድርግ!” አለው።
38
በጉዞአቸውም ላይ ሳሉ እርሱ ወደ አንዲት መንደር ገባ፤ ማርታ የተባለች አንዲት ሴትም በቤትዋ ተቀበለችው።
39
ለእርሷም ማርያም የምትባል እኅት ነበረቻት፤ እርሷም ደግሞ በኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጣ ቃሉን ትሰማ ነበር።
40
ማርታ ግን አገልግሎት ስለ በዛባት ባከነች፤ ቀርባም፦ “ጌታ ሆይ! እኅቴ ብቻዬን እንዳገለግል ስትተወኝ አይገድህምን? እንግዲያውስ እንድታግዘኝ ንገራት፤” አለችው።
41
ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላት፦ “ማርታ! ማርታ! በብዙ ነገር ትጨነቂአለሽ ትታወኪያለሽም፤
42
የሚያስፈልገው ግን አንድ ነገር ብቻ ነው፤ ማርያምም መልካሙን ድርሻ መርጣለች፤ ከእርሷም አይወሰድባትም።”
← Chapter 9
Chapter 11 →