bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic Catholic Version (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)) No Year
/
John 20
John 20
Amharic Catholic Version (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)) No Year
1
ከሳምንቱም በመጀመሪያው ቀን መግደላዊት ማርያም ገና ጨለሞ ሳለ በማለዳ ወደ መቃብር መጣች፤ ድንጋዩም ከመቃብሩ ተፈንቅሎ አየች።
2
እየሮጠችም ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ይወደው ወደነበረው ወደ ሌላው ደቀመዝሙር መጥታ “ጌታን ከመቃብር ወስደውታል፤ የት እንዳኖሩትም አናውቅም” አለቻቸው።
3
ስለዚህ ጴጥሮስና ሌላው ደቀመዝሙር ወጥተው ወደ መቃብሩ ሄዱ።
4
ሁለቱም አብረው ሮጡ፤ ሌላው ደቀ መዝሙርም ከጴጥሮስ ይልቅ ፈጥኖ ወደ ፊት ሮጠና ቀድሞ ወደ መቃብሩ ደረሰ፤
5
ዝቅም ብሎ ሲመለከት የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፤ ነገር ግን አልገባም።
6
ስምዖን ጴጥሮስም ተከትሎት መጣ፤ ወደ መቃብሩም ገባ፤ የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፤
7
እንዲሁም በራሱ ላይ የነበረውን ጨርቅ ለብቻው በአንድ ስፍራ ተጠምጥሞ እንደ ነበረ እንጂ ከተልባ እግሩ ልብስ ጋር ተቀምጦ እንዳልነበረ አየ።
8
በዚያን ጊዜ አስቀድሞ ወደ መቃብር የመጣውም ሌላው ደቀመዝሙር ገባ፤ አየም፤ አመነም፤
9
“ከሙታን መነሣት ይገባዋል” የሚለውን የመጽሐፉን ቃል ገና አላወቁም ነበርና።
10
ደቀ መዛሙርቱም ወደ ቤታቸው ሄዱ።
11
ማርያም ግን እያለቀሰች ከመቃብሩ በስተ ውጭ ቆማ ነበር። እያለቀሰችም ወደ መቃብር ዝቅ ብላ ተመለከተች፤
12
ሁለት ነጭ ልብስ የለበሱ መላእክትም፥ የኢየሱስን ሥጋ አስተኝተውበት በነበረበት ስፍራ፥ አንዱ በራስጌ ሌላውም በእግርጌ ተቀምጠው አየች።
13
እነርሱም “አንቺ ሴት! ስለምን ታለቅሻለሽ?” አሉአት። እርሷም “ጌታዬን ወስደውታል፤ ወዴትም እንዳኖሩት አላውቅም፤” አለቻቸው።
14
ይህንም ብላ ወደ ኋላ ዘወር ስትል ኢየሱስን ቆሞ አየችው፤ ነገር ግን ኢየሱስ እንደሆነ አላወቀችም።
15
ኢየሱስም “አንቺ ሴት! ስለምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊያለሽ?” አላት። እርሷም የአትክልት ጠባቂ መስሎአት “ጌታ ሆይ! አንተ ወስደኸው እንደሆንህ ወዴት እንዳኖርኸው ንገረኝ፤ እኔም እወስደዋለሁ፤” አለችው።
16
ኢየሱስም “ማርያም!” አላት። እርሷ ዘወር ብላ በዕብራይስጥ “ረቡኒ!” አለችው፤ ትርጓሜውም “መምህር ሆይ!” ማለት ነው።
17
ኢየሱስም “ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ ‘እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዐርጋለሁ፤’ ብለሽ ንገሪአቸው፤” አላት።
18
መግደላዊት ማርያም ሄደችና ጌታን እንዳየችው፥ ይህንንም እንዳላት ለደቀ መዛሙርቱ ነገረች።
19
በዚያው ከሳምንቱ የመጀመሪያው በሆነው ቀን፥ በመሸ ጊዜ፥ ደቀመዛሙርቱ ተሰብስበው በነበሩበት፥ አይሁድን ስለ ፈሩ ደጆቹ ተዘግተው ሳሉ፥ ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው።
20
ይህንንም ብሎ እጆቹንም ጎኑንም አሳያቸው። ደቀ መዛሙርቱም ጌታን ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው።
21
ኢየሱስም ዳግመኛ “ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ፤” አላቸው።
22
ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ።
23
ኀጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል፤” አላቸው።
24
ነገር ግን ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ዲዲሞስ የሚሉት ቶማስ ኢየሱስ በመጣ ጊዜ ከእነርሱ ጋር አልነበረም።
25
ሌሎቹም ደቀመዛሙርቱ “ጌታን አይተነዋል፤” አሉት። እርሱ ግን “የችንካሩን ምልክት በእጆቹ ላይ ካላየሁ፥ ጣቴንም በችንካሩ ምልክት ውስጥ ካላስገባሁ፥ እጄንም በጎኑ ቊስል ውስጥ ካላስገባሁ አላምንም፤” አላቸው።
26
ከስምንት ቀን በኋላም ደቀመዛሙርቱ ደግመው በቤት ውስጥ ነበሩ፤ ቶማስም ከእነርሱ ጋር ነበረ። ደጆቹ ተዘግተው ሳሉ ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው።
27
ከዚያም በኋላ ቶማስን “ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ ውስጥ አስገባው፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን፤” አለው።
28
ቶማስም “ጌታዬና አምላኬ!” ብሎ መለሰለት።
29
ኢየሱስም “ስለ አየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው” አለው።
30
ኢየሱስም በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፉ ሌላ ብዙ ምልክቶችን በደቀ መዛሙርቱ ፊት አደረገ፤
31
ነገር ግን ኢየሱስ መሢሕ፥ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎአል።
← Chapter 19
Chapter 21 →