bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic 2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
/
Luke 18
Luke 18
Amharic 2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
1
ዘወትር እንዲጸልዩ፥ እንዳይሰለቹም በምሳሌ ነገራቸው።
2
እንዲህም አላቸው፥ “በአንዲት ከተማ እግዚአብሔርን የማይፈራ፥ ሰውንም የማያፍር አንድ ዳኛ ነበር።
3
በዚያችም ከተማ አንዲት መበለት ነበረች፤ ዕለት ዕለትም ወደ እርሱ እየመጣች ከባለጋራዬ ፍረድልኝ ትለው ነበር።
4
እንቢ ብሎም አዘገያት። ከዚህም በኋላ በልቡ ዐስቦ እንዲህ አለ፦ ‘ምንም እግዚአብሔርን ባልፈራ፥ ሰውንም ባላፍር
5
ይህቺ ሴት እንዳትዘበዝበኝ፥ ዘወትርም እየመጣች እንዳታታክተኝ እፈርድላታለሁ’።”
6
ጌታችንም እንዲህ አላቸው፥ “ዐመፀኛው ዳኛ ያለውን ስሙ።
7
እንግዲህ እግዚአብሔር በመዓልትና በሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ ለወዳጆቹ አይፈርድምን? ወይስ ቸል ይላቸዋልን?
8
እላችኋለሁ ፈጥኖ ይፈርድላቸዋል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር ላይ እምነትን ያገኝ ይሆን?”
9
ራሳቸውን ለሚያመጻድቁና ባልንጀራቸውን ለሚንቁ እንዲህ ብሎ መሰለላቸው።
10
“ሁለት ሰዎች ሊጸልዩ ወደ ቤተ መቅደስ ወጡ፤ አንዱ ፈሪሳዊ፥ ሁለተኛውም ቀራጭ ነበር።
11
ፈሪሳዊውም ቆመና እንዲህ ብሎ ጸለየ፦ ‘አቤቱ እንደ ሌሎች ሰዎች፥ እንደ ቀማኞችና እንደ ዐመፀኞች፥ እንደ አመንዝሮችም፥ ወይም እንደዚህ ቀራጭ ያላደረግኸኝ አመሰግንሃለሁ።
12
እኔ በየሳምንቱ ሁለት ቀን እጾማለሁ፤ ከማገኘውም ሁሉ ከዐሥር አንድ እሰጣለሁ።’
13
ቀራጩ ግን ራቅ ብሎ ቆመ፤ ዐይኖቹንም ወደ ላይ ወደ ሰማይ ሊያነሣ አልወደደም፤ ደረቱንም እየመታ፦ ‘አቤቱ፥ እኔን ኀጢኣተኛውን ይቅር በለኝ’ አለ።
14
እላችኋለሁ፥ ከዚያ ይልቅ ይህ ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፤ ራሱንም የሚያዋርድ ይከብራልና።”
15
ይባርካቸውም ዘንድ ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡአቸው፤ ደቀ መዛሙርቱም አይተው ገሠጹአቸው።
16
ጌታችን ኢየሱስም ጠራቸው፤ እንዲህም አላቸው፥ “ሕፃናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉአቸው፥ አትከልክሉአቸውም፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና።
17
እውነት እላችኋለሁ፥ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃናት ያልተቀበላት አይገባባትም።”
18
አንድ አለቃም፥ “ቸር መምህር፥ ምን ሥራ ሠርቼ የዘለዓለም ሕይወትን እወርሳለሁ?” አለው።
19
ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አለው፥ “ለምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር የለም።
20
ትእዛዛቱን አንተ ራስህ ታውቃለህ፤ ‘አትግደል፤ አታመንዝር፤ አትስረቅ፤ በሐሰት አትመስክር፤ አባትህንና እናትህንም አክብር።’
21
እርሱም፦ ‘ይህንስ ሁሉ ከልጅነቴ ጀምሬ እስከ ዛሬ ጠብቄአለሁ’።” አለው።
22
ጌታችን ኢየሱስም ይህን ሰምቶ እንዲህ አለው፥ “አንዲት ቀርታሃለች፤ ሂድና ያለህን ሁሉ ሸጠህ ለነዳያን ስጥ፤ በሰማይም መዝገብ ታገኛለህ፤ መጥተህም ተከተለኝ።”
23
እርሱ ግን ይህን ሰምቶ በጣም አዘነ፤ እርሱ እጅግ ባለጸጋ ነበርና።
24
ጌታችን ኢየሱስም እጅግ ሲያዝን አይቶ እንዲህ አለ፥ “ገንዘብ ላላቸው ሰዎች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው!
25
ባለጸጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ሊያልፍ ይቀላል።”
26
የሰሙትም፥ “እንግዲህ ማን ሊድን ይችላል?” አሉ።
27
እርሱ ግን “በሰው ዘንድ የማይቻለው በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል” አላቸው።
28
ጴጥሮስም፥ “እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከትለንሃል፤ እንግዲህ ምን እናገኛለን?” አለው።
29
እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “እውነት እላችኋለሁ፥ ቤቱንና ዘመዶቹን፥ ወንድሞቹንና ሚስቱን፥ ልጆቹንም ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የሚተው፥
30
በዚህ ዓለም መቶ እጥፍ ዋጋ፥ በሚመጣውም ዓለም የዘለዓለም ሕይወትን የማይቀበል ማንም የለም።”
31
ዐሥራ ሁለቱንም ወሰዳቸው፤ እንዲህም አላቸው፥ “እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፤ በነቢያትም የተጻፈው ሁሉ በሰው ልጅ ላይ ይፈጸማል።
32
ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፤ ይዘብቱበታልም፤ ይሰድቡታልም፤ ይተፉበታልም።
33
ይገርፉታል፤ ይገድሉታልም፤ በሦስተኛዪቱም ቀን ይነሣል።”
34
እነርሱ ግን፤ ከተናገራቸው ያስተዋሉት የለም፤ ይህ ነገር ከእነርሱ የተሰወረ ነበርና፤ የተናገረውንም አያውቁም ነበርና።
35
ከዚህም በኋላ ኢያሪኮ በደረሱ ጊዜ አንድ ዕውር በጎዳና ተቀምጦ ይለምን ነበር።
36
የሚያልፈውንም ሰው ድምፅ ሰምቶ፥ “ይህ የምሰማው ምንድን ነው?” አለ።
37
እነርሱም፥ “የናዝሬቱ ኢየሱስ ያልፋል” ብለው ነገሩት።
38
ድምፁንም ከፍ አድርጎ፥ “የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ማረኝ” አለ።
39
የሚመሩትም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን በጣም ጮኾ፥ “የዳዊት ልጅ ሆይ፥ ማረኝ” አለ።
40
ጌታችን ኢየሱስም ቆመና ወደ እርሱ እንዲያመጡት አዘዘ።
41
ወደ እርሱም በደረሰ ጊዜ፥ “ምን ላደርግልህ ትወዳለህ?” ብሎ ጠየቀው፤ እርሱም፥ “ጌታ ሆይ፥ ዐይኖች እንዲያዩ ነው” አለው።
42
ጌታችን ኢየሱስም፥ “እይ፤ እምነትህ አዳነችህ” አለው።
43
በዚያን ጊዜም አየ፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነ፤ ተከተለውም፤ ሕዝቡም ሁሉ አይተው እግዚአብሔርን አመሰገኑት።
← Chapter 17
Chapter 19 →