bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic 2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
/
Isaiah 57
Isaiah 57
Amharic 2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
1
ጻድቅ ሰው እንደጠፋ አያችሁ፤ ይህንም በልባችሁ አላሰባችሁም፤ ጻድቃን ሰዎች ይወገዳሉ፤ ጻድቅም ከክፋት ፊት እንደ ተወገደ ማንም አያስተውልም።
2
መቃብሩ በሰላም ይሆናል፤ ከመካከልም ይወሰዳል።
3
እናንተ የኃጥኣን ልጆች፥ የዘማውያንና የጋለሞታዪቱ ዘር፥ ወደዚህ ቅረቡ።
4
በማን ታላግጣላችሁ? በማንስ ላይ አፋችሁን ታላቅቃላችሁ? ምላሳችሁንስ በማን ላይ ታስረዝማላችሁ?
5
እናንተ በለመለመ ዛፍ ሁሉ በታች በጣዖት ደስ የምትሰኙ፥ እናንተም በሸለቆች ውስጥ በዓለትም ስንጣቂዎች በታች ልጆቻችሁን የምትሠዉ፥ እናንተ የጥፋት ልጆችና የዐመፀኞች ዘሮች አይደላችሁምን?
6
በሸለቆ ውስጥ ያሉ የለዘቡ ድንጋዮች ዕድል ፋንታሽ ናቸው፤ እነርሱም ዕጣሽ ናቸው፤ ለእነርሱም የመጠጥ ቍርባን አፍስሰሻል፤ የእህልንም ቍርባን አቅርበሻል። እንግዲህ በዚህ ነገር አልቈጣምን?
7
ከፍ ባለውና በረዘመውም ተራራ ላይ መኝታሽን አደረግሽ፤ በዚያም መሥዋዕትሽን ሠዋሽ።
8
ከመዝጊያው በኋላ መታሰቢያሽን አደረግሽ፤ እኔን ብትተዪ የሚጠቅምሽ መሰለሽን? ከእኔም ይልቅ ከአንቺ ጋራ የሚተኙትን መረጥሽ።
9
ዝሙትሽን ከእነርሱ ጋር አበዛሽ፤ ከአንቺ የራቁ ብዙዎችንም ተጐዳኘሽ። መልእክተኞችሽንም ወደ ሩቅ ላክሽ፤ ከእነርሱም ጋር ተወገድሽ፤ እስከ ሲኦልም ድረስ ተዋረድሽ።
10
በመንገድሽም ብዛት ደከምሽ፤ ዳግመኛም ጕልበት እያለኝ ከእንግዲህ ወዲህ ይህን መንገድ አልተውም አላልሽም፤ ይህንም ስላደረግሽ አላፈርሽም።
11
ሐሰት የተናገርሽው፥ እኔንም ያላሰብሽው፥ በልብሽም ነገሩን ያላኖርሽው ማንን ሰግተሽ ነው? ማንንስ ፈርተሽ ነው? እኔም ዝም አልሁሽ፤ አንቺም አልፈራሽኝም።
12
እንግዲህ እኔ ጽድቄንና የማይረባሽን የአንቺን በደል እናገራለሁ።
13
በችግርሽ ቀን በጮኽሽ ጊዜ እስኪ ይታደጉሽ፤ እነሆ፥ ዐውሎ ይወስዳቸዋል፤ ነፋስም ሁሉን ያስወግዳቸዋል። ወደ እኔ የሚጠጉ ግን ምድሪቱን ይገዛሉ፤ የተቀደሰውን ተራራዬንም ይወርሳሉ።
14
እርሱም፥ “በፊቱ፥ መንገድን ጥረጉ፤ ከሕዝቤም መንገድ ዕንቅፋትን አስወግዱ” ይላል።
15
ለዘለዓለም በአርያም የሚኖር ስሙም ቅዱሰ ቅዱሳን የሆነ፥ በቅዱሳን አድሮ የሚኖር፥ ለተዋረዱት ትዕግሥትን የሚሰጥ፥ ልባቸውም ለተቀጠቀጠ ሕይወትን የሚሰጥ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
16
“መንፈስ ከእኔ ይወጣልና፥ የሁሉንም ነፍስ ፈጥሬአለሁና ለዘለዓለም አልቀስፋችሁም፤ ሁልጊዜም አልቈጣችሁም።
17
ስለ ኀጢአቱ ጥቂት ጊዜ መከራ አመጣሁበት፤ ቀሠፍሁትም፤ ፊቴንም ከእርሱ መለስሁ፤ እርሱም አዘነ። እያዘነም ሄደ።
18
ከዚህም በኋላ መንገዱን አይቻለሁ፤ ፈወስሁትም፤ አጽናናሁት፤ እውነተኛ ደስታንም ሰጠሁት።
19
በሩቅም በቅርብም ላሉ በሰላም ላይ ሰላም ይሁን፤ እፈውሳቸውማለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
20
“ኃጥኣን ግን እንዲህ ይገለበጣሉ፤ ዕረፍትንም አያገኙም።
21
ለኃጥአን ደስታ የላቸውም” ይላል እግዚአብሔር።
← Chapter 56
Chapter 58 →