bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic 2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
/
Exodus 36
Exodus 36
Amharic 2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
1
“ባስልኤልና ኤልያብ፥ ለመቅደስም ማገልገያ ሥራ ሁሉ ያደርጉ ዘንድ እንዲያውቁ እግዚአብሔር ጥበብንና ማስተዋልን የሰጣቸው በልባቸውም ጥበበኞች የሆኑ ሁሉ እግዚአብሔር ያዘዘውን ነገር ሁሉ አደረጉ።”
2
ሙሴም ባስልኤልንና ኤልያብን፥ እግዚአብሔርም ዕውቀትንና ጥበብን በልቡናቸው ያሳደረባቸውንና ጥበብ ያላቸውን፥ ሥራውንም ለመሥራት ይቀርብ ዘንድ ልቡ ያስነሣውን ሁሉ ሥራውን ሠርተው ይፈጽሙ ዘንድ ጠራቸው።
3
እነርሱም የእስራኤል ልጆች ለመቅደስ ማገልገያ ሥራ ያመጡትን ስጦታ ሁሉ ይሠሩ ዘንድ ከሙሴ ተቀበሉ። እነዚያም እንደ ፈቃዳቸው ማለዳ ማለዳ ስጦታውን ገና ወደ እርሱ ያመጡ ነበር።
4
እያንዳንዳቸው በሚሠሩት የመቅደሱን ሥራ የሚሠሩ ጠቢባን ሁሉ መጡ፤
5
እነርሱም ለሙሴ፥ “እግዚአብሔር ይደረግ ዘንድ ላዘዘው ሥራ ከሚበቃ በላይ እጅግ የሚበልጥ ሕዝቡ አመጡ” ብለው ነገሩት።
6
ሙሴም አዘዘና፥ “ወንድ ወይም ሴት ለመቅደስ ስጦታ ከዚህ የበለጠ የሚያመጣ አይኑር” ብሎ በሰፈሩ ውስጥ አወጀ። ሕዝቡም እንዳያመጡ ተከለከሉ።
7
ያመጡትም ነገር ሥራን ሁሉ ለመፈጸም በቅቶ ገና ይተርፍ ነበረና።
8
በእነርሱም ዘንድ ያሉት፥ ሥራ ሲሠሩ የነበሩት በልባቸው ጥበበኞች ሁሉ ድንኳኑን ከዐሥር መጋረጃዎች ሠሩ፤ እነርሱንም ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ፥ ከሰማያዊም፥ ከሐምራዊም፥ ከቀይም ግምጃ ሠሩ፤ በእነርሱም ላይ በጥልፍ ሥራ ኪሩቤልን አደረጉባቸው።
9
የእያንዳንዱ መጋረጃ ርዝመት ሃያ ስምንት ክንድ፥ ወርዱም አራት ክንድ ነበረ፤ የመጋረጃዎቹ ሁሉ ልክ ትክክል ነበረ።
10
አምስቱንም መጋረጃዎች እርስ በርሳቸው አንዱን ከሌላው ጋር አጋጠሙ፤ አምስቱንም መጋረጃዎች እርስ በርሳቸው እንዲሁ አጋጠሙ።
11
ከሚጋጠሙትም መጋረጃዎች በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ የሰማያዊውን ግምጃ ቀለበቶች አደረጉ፤ ደግሞ ከተጋጠሙት ከሌሎቹ በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ እንዲሁ አደረጉ።
12
አምሳ ቀለበቶችን በአንድ መጋረጃ አደረጉ፤ አምሳውንም ቀለበቶች በሁለተኛው መጋረጃ ዘርፍ አደረጉ፤ ቀለበቶቹ እርስ በርሳቸው ፊት ለፊት የሚተያዩ ነበሩ።
13
አምሳም የወርቅ መያዣዎችን ሠሩ፤ መጋረጃዎችንም አንዱን ከሌላው በመያዣዎች አጋጠሙአቸው፤ አንድ ድንኳንም ሆነ።
14
ከድንኳኑም በላይ የሚሆኑ መጋረጃዎችን ከፍየል ጠጕር አደረጉ፤ ዐሥራ አንድ መጋረጃዎችንም አደረጉ።
15
እያንዳንዱም መጋረጃ ርዝመቱ ሠላሳ ክንድ፥ እያንዳንዱም መጋረጃ ወርዱ አራት ክንድ ነበረ፤ የእያንዳንዱም መጋረጃ መጠኑ ትክክል ነበረ።
16
አምስቱንም መጋረጃዎች እርስ በርሳቸው አንድ አደረጉ፤ ስድስቱንም መጋረጃዎች አንድ አድርገው አጋጠሙአቸው።
17
ከተጋጠሙትም መጋረጃዎች በአንደኛው መጋረጃ ጠርዝ ላይ አምሳ ቀለበቶችን አደረጉ፤ እንዲሁም በሁለተኛው መጋረጃ ጠርዝ በሚጋጠሙበት በኩል አምሳ ቀለበቶችን አደረጉ።
18
ድንኳኑም አንድ እንዲሆን ያጋጥሙት ዘንድ አምሳ የናስ መያዣዎችን ሠሩ።
19
ለድንኳኑም መደረቢያ ከቀይ አውራ በግ የተለፋ ቍርበት፥ ከዚያም በላይ ሌላ መደረቢያ ከአቆስጣ ቍርበት አደረጉ።
20
ለድንኳኑም ከማይነቅዝ ዕንጨት የሚቆሙትን ሳንቆች አደረጉ።
21
የሳንቃው ሁሉ ርዝመቱ ዐሥር ክንድ፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል ነበረ።
22
ለእያንዳንዱም ሳንቃ አንዱን በአንዱ ላይ የሚያያይዙ ሁለት ማጋጠሚያዎች ነበሩ፤ ለድንኳኑም ሳንቆች ሁሉ እንዲሁ አደረጉ።
23
ለድንኳኑም በደቡብ ወገን ሃያ ሳንቆችን አደረጉ፤
24
ከሃያውም ሳንቆች በታች አርባ የብር እግሮች አደረጉ፤ ከእያንዳንዱም ሳንቃ በታች ለሁለቱ ማጋጠሚያዎች ሁለት እግሮች ነበሩ።
25
ለድንኳኑም ለሁለተኛው ወገን በሰሜን በኩል ሃያ ሳንቆች አደረጉ፤
26
ለእነርሱም አርባ የብር እግሮች፥ ከእያንዳንዱም ሳንቃ በታች ሁለት እግሮች አደረጉ።
27
ለድንኳኑም በምዕራቡ ወገን በስተኋላ ስድስት ሳንቆች አደረጉ።
28
ለድንኳኑም ለሁለቱ ማዕዘን በስተኋላ ሁለት ሳንቆች አደረጉ።
29
ከታችም እስከ ላይ እስከ አንደኛው ቀለበት ድረስ አንድ ሳንቃ ድርብ ነበረ፤ ለሁለቱም ማዕዘን እንዲሁ ሁለት ነበሩ።
30
ስምንት ሳንቆችና ዐሥራ ስድስቱ የብር እግሮቻቸው፥ ከእያንዳንዱም ሳንቃ በታች ሁለት ሁለት እግሮች ነበሩ።
31
ከማይነቅዝ ዕንጨት በድንኳኑ በአንደኛው ወገን ላሉት ሳንቆች አምስት መወርወሪያዎችን፥
32
በድንኳኑም በሁለተኛው ወገን ላሉት ሳንቆች አምስት መወርወሪያዎችን፥ ከድንኳኑም በስተኋላ በምዕራቡ ወገን ላሉት ሳንቆች አምስት መወርወሪያዎችን አደረጉ።
33
መካከለኛውንም መወርወሪያ በሳንቆቹ መካከል ከዳር እስከ ዳር እንዲያልፍ አደረጉ።
34
ሳንቆቹንም በወርቅ ለበጡአቸው፤ ቀለበቶቻቸውንም የመወርወሪያ ቤት እንዲሆኑላቸው ከወርቅ አደረጉ፤ መወርወሪያዎቹንም በወርቅ ለበጡአቸው።
35
መጋረጃውንም ከሰማያዊና ከሐምራዊ፥ ከቀይም ግምጃ፥ ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ አደረጉ፤ ኪሩቤልንም በጥልፍ ሥራ በእርሱ ላይ አደረጉ።
36
ከማይነቅዝም ዕንጨት አራት ምሰሶዎች አደረጉለት፤በወርቅም ለበጡአቸው፤ ኵላቦቻቸውም የወርቅ ነበሩ፤ ለእነርሱም አራት የብር እግሮች አደረጉ።
37
ለድንኳኑም ደጃፍ ከሰማያዊና ከሐምራዊ፥ ከቀይም ግምጃ፥ ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ በጥልፍ አሠራር የተሠራ መጋረጃ አደረጉ፤
38
አምስቱንም ምሰሶዎች፥ ኵላቦቻቸውንም አደረጉ፤ ጉልላቶቻቸውንና ዘንጎቻቸውንም በወርቅ ለበጡአቸው፤ አምስቱም እግሮቻቸው የናስ ነበሩ።
← Chapter 35
Chapter 37 →