bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic 2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
/
Deuteronomy 33
Deuteronomy 33
Amharic 2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
1
የእግዚአብሔር ሰው ሙሴ ሳይሞት የእስራኤልን ልጆች የባረከባት በረከት ይህች ናት።
2
እንዲህም አለ፦ “እግዚአብሔር ከሲና መጣ፤ በሴይርም ተገለጠልን፤ ከፋራን ተራራ፥ ከቃዴስ አእላፋት ጋር ፈጥኖ መጣ፤ መላእክቱም ከእርሱ ጋር በቀኙ ነበሩ።
3
ለሕዝቡም ራራላቸው፤ ቅዱሳን ሁሉ ከእጅህ በታች ናቸው፤ እነርሱም የአንተ ናቸው። ቃሎችህንም ይቀበላሉ።
4
ሙሴም ለያዕቆብ ማኅበር ርስት የሆነውን ሕግ አዘዘን።
5
የሕዝቡ አለቆች ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ ጋር በተሰበሰቡ ጊዜ፥ አለቃ በተወዳጁ ዘንድ ይሆናል።
6
ሮቤልን እፈልገዋለሁ፤ አይሙትብኝ፤ ቍጥሩም ብዙ ይሁን።
7
የይሁዳም በረከት ይህች ናት፤ አቤቱ የይሁዳን ቃል ስማ፤ ወደ ሕዝቡም ይግባ፤ እጆቹም ይግዙ፤ በጠላቶቹ ላይ ረዳት ትሆነዋለህ።
8
ስለ ሌዊም እንዲህ አለ፥ ለሌዊ ቃሉን፥ በመከራም ለፈተኑት፥ በክርክር ውኃም ለሰደቡት፥ ለእውነተኛው ሰው ጽድቁን መልስ።
9
እናቱንና አባቱን አላየኋችሁም ላለ፥ ወንድሞቹንም ላላወቀ፥ ልጆቹንም ላላስተዋለ፤ ቃልህን ለጠበቀ፥ በቃል ኪዳንህም ለተማጠነ።
10
ፍርድህን ለያዕቆብ፥ ሕግህንም ለእስራኤል ያስተምራሉ፤ በማዕጠንትህ ዕጣንን፥ በመሠዊያህም የሚቃጠል መሥዋዕትን ሁልጊዜ ያቀርባሉ።
11
አቤቱ ኀይሉን ባርክ፤ የእጁንም ሥራ ተቀበል፤ በሚቃወሙት ጠላቶቹ ላይ መከራን አውርድ፤ የሚጠሉትም አይነሡ።
12
ስለ ብንያምም እንዲህ አለ፦ በእግዚአብሔር የተወደደ በእርሱ ዘንድ ተማምኖ ይኖራል፤ እግዚአብሔርም በዘመኑ ሁሉ ይጋርደዋል፤ በትከሻውም መካከል ያድራል።
13
ስለ ዮሴፍም እንዲህ አለ፦ ምድሩ ከእግዚአብሔር በረከት፥ ከሰማይ ዝናምና ጠል፥ ከታችም ከጥልቁ ምንጭ ናት።
14
ከፀሐይ መውጣት ከሚገኘው ፍሬ፥ በወራት ቍጥር ከሚገኘው ምርት፥
15
ከቀደሙትም ተራሮች ከፍተኛነት፥ ከዘለዓለሙ ኮረብቶች ራሶች፥
16
በየወቅቱም ከምድሪቱ ምላት፥ በቍጥቋጦው ውስጥ ከነበረው በረከት፥ በዮሴፍ ራስ ላይ፥ ከወንድሞቹም በከበረው በእርሱ ራስ ላይ ይውረድ።
17
ውበቱ እንደ ላም በኵር ነው፤ ቀንዶቹ አንድ ቀንድ እንዳለው ናቸው፤ በእነርሱ እስከ ምድር ዳርቻ ያሉትን አሕዛብ ሁሉ ይወጋል፤ የኤፍሬም እልፍ አእላፋት፥ የምናሴም አእላፋት እነርሱ ናቸው።
18
ስለ ዛብሎንም እንዲህ አለ፦ ዛብሎን ሆይ፥ በመውጣትህ፥ ይሳኮር ሆይ፥ በድንኳንህ ውስጥ ደስ ይበላችሁ።
19
አሕዛብን ያጠፉአቸዋል፤ በዚያም ይጠሩአቸዋል፤ የጽድቅ መሥዋዕትንም ይሠዋሉ፤ የባሕሩም ሀብት፥ በባሕሩ ዳር የሚኖሩ ሰዎችም ገንዘብ ይመግብሃልና፥
20
ስለ ጋድም እንዲህ አለ፦ ጋድን ሰፊ ያደረገ ቡሩክ ይሁን፤ እንደ አንበሳ ያለቆችን ክንድ ቀጥቅጦ ያርፋል።
21
በዚያ ከሕዝቡ ገዦች ጋር የተሰበሰቡ የአለቆች ምድር እንደ ተከፈለች፥ የመጀመሪያውን ፍሬ አየ፤ እግዚአብሔርም ጽድቁን፥ ፍርዱንም ከእስራኤል ጋር አደረገ።
22
ስለ ዳንም እንዲህ አለ፦ ዳን የአንበሳ ደቦል ነው፤ ከባሳን ይበርራል።
23
ስለ ንፍታሌምም እንዲህ አለ፦ ንፍታሌም ከበጎ ነገር ጠግቦአል፤ የእግዚአብሔርንም በረከት ተሞልቶአል፤ ባሕርንና ሊባን ይወርሳል።
24
ስለ አሴርም እንዲህ አለ፦ አሴር ከልጆች የተነሣ የተባረከ ይሁን፤ ለወንድሞቹም የተመረጠ ይሁን፤ እግሩንም በዘይት ያጥባል።
25
ጫማህ ብረትና ናስ ይሆናል፤ እንደ ዕድሜህ እንዲሁ ኀይልህ ይሆናል።
26
እንደ ፍቁሩ አምላክ ማንም የለም፤ በሰማይ የሚኖረው፥ በጠፈርም በታላቅነት ያለው እርሱ ረዳትህ ነው።
27
እግዚአብሔርም ፊት ለፊት፥ በዘለዓለም ክንዶች ኀይል ይጋርድሃል፤ ጠላትህን ከፊትህ አውጥቶ፦ አጥፋው ይላል።
28
እስራኤልም ተማምኖ፥ በያዕቆብ ምድር ብቻውን፥ በስንዴና በወይን ምድር ይኖራል፤ ሰማይ ከደመናና ከጠል ጋር ለአንተ ነው።
29
እስራኤል ሆይ ብፁዕ ነህ፤ በእግዚአብሔር የዳነ ሕዝብ እንደ አንተ ማንነው? እርሱ ያጸንሃል፤ ይረዳሃልም፤ ትምክሕትህ በሰይፍህ ነው፤ ጠላቶችህ ውሸታሞች ናቸው፤ አንተም በአንገታቸው ላይ ትጫናለህ።”
← Chapter 32
Chapter 34 →