bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic 2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
/
2 Samuel 5
2 Samuel 5
Amharic 2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
1
የእስራኤልም ነገድ ሁሉ ወደ ኬብሮን ወደ ዳዊት መጥተው እንዲህ አሉት፥ “እኛ የአጥንትህ ፍላጭ የሥጋህ ቍራጭ ነን።
2
አስቀድሞ ሳኦል በእኛ ላይ ንጉሥ ሆኖ ሳለ እስራኤልን የምታወጣና የምታገባ አንተ ነበርህ፤ እግዚአብሔርም፦ አንተ ሕዝቤን እስራኤልን ትጠብቃለህ፤ በእስራኤልም ላይ አለቃ ትሆናለህ ብሎህ” ነበር።
3
የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ ወደ ንጉሡ ወደ ኬብሮን መጡ፤ ንጉሡ ዳዊትም በኬብሮን በእግዚአብሔር ፊት ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፤ በእስራኤልም ንጉሥ ይሆን ዘንድ ዳዊትን ቀቡት።
4
ዳዊትም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሠላሳ ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ አርባ ዓመትም ነገሠ፤
5
በኬብሮን በይሁዳ ላይ ሰባት ዓመት ከስድስት ወር ነገሠ፤ በኢየሩሳሌምም በእስራኤል ሁሉና በይሁዳ ላይ ሠላሳ ሦስት ዓመት ነገሠ።
6
ዳዊትና ሰዎቹም በሀገሩ ውስጥ ወደሚኖሩት ወደ ኢያቡሴዎናውያን ወደ ኢየሩሳሌም ሄዱ፤ እነርሱም ዳዊትን፥ “ወደዚህ አትገባም” አሉት። ዕውሮችና አንካሶችም ወደዚህ አትገባም ብለው ተቃወሙት።
7
ነገር ግን ዳዊት አንባዪቱን ጽዮንን ያዘ፤ እርስዋም የዳዊት ከተማ ናት።
8
በዚያም ቀን ዳዊት፥ “ኢያቡሴዎናውያንን የሚመታ ሁሉ፥ ዕውሮችንና አንካሶችን፥ የዳዊትንም ነፍስ የሚጠሉትን ሁሉ በሳንጃ ይውጋቸው” አለ። ስለዚህም፥ “ዕውርና አንካሳ ወደ እግዚአብሔር ቤት አይግቡ” ተባለ።
9
ዳዊትም በአንባዪቱ ውስጥ ተቀመጠ፤ እርስዋም የዳዊት ከተማ ተባለች። ከተማዋንም ዙሪያዋን እስከ ዳርቻዋ ድረስ ቀጠራት፤ ቤቱንም ሠራ።
10
ዳዊትም እየበረታ፥ ከፍ እያለም ሄደ፤ ሁሉን የሚችል እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ።
11
የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ወደ ዳዊት መልእክተኞችን፥ የዝግባ እንጨትንም፥ አናጢዎችንም፥ ድንጋይ ጠራቢዎችንም ላከ፤ ለዳዊትም ቤት ሠሩለት።
12
ዳዊትም እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርጎ እንዳዘጋጀው፥ ስለ ሕዝቡ ስለ እስራኤልም መንግሥቱን ከፍ እንዳደረገ ዐወቀ።
13
ዳዊትም ከኬብሮን ከመጣ በኋላ እንደ ገና ቁባቶቹንና ሚስቶቹን ከኢየሩሳሌም ወሰደ፤ ለዳዊትም ደግሞ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ተወለዱለት።
14
በኢየሩሳሌምም የተወለዱለት ስማቸው ይህ ነው፤ ሳሚስ፥ ሶባብ፥ ናታን፥ ሰሎሞን፥
15
ኢያቢሖር፥ ኤሊሱስ፥ ናፌቅ፥ ያፍያ፥
16
ኤሊሳማ፥ ኤሊዳሂ፥ ኤሊፋላት፥ ሶሜኤ፥ ኢያሴቦት፥ ናታን፥ ጋላማሄን፥ የበአር፥ ትሄሱስ፥ ኤልፋላት፥ ናጌድ፥ ናሬት፥ ያናታ፥ ሊሳሚስ፥ በአሊማት፥ ኤልፋላድ።
17
ፍልስጥኤማውያንም ዳዊት በእስራኤል ላይ ንጉሥ ሆኖ እንደ ተቀባ ሰሙ፤ ፍልስጥኤማውያንም ሁሉ ዳዊትን ሊፈልጉ ወጡ፤ ዳዊትም በሰማ ጊዜ ወደ ምሽጉ ወረደ።
18
ፍልስጥኤማውያንም መጥተው በረዓይት ሸለቆ ተበትነው ሰፈሩ።
19
ዳዊትም፥ “ወደ ፍልስጥኤማውያን ልውጣን? በእጄስ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህን?” ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም ዳዊትን፥ “ፍልስጥኤማውያንን በርግጥ በእጅህ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁና ውጣ” አለው።
20
ዳዊትም ከላይኛው መጋደያ መጣ፤ በዚያም መታቸውና፥ “ውኃ እንደሚያጠፋ እግዚአብሔር ጠላቶቼን ፍልስጥኤማውያንን በፊቴ አጠፋቸው” አለ። ስለዚህም የዚያ ስፍራ ስም “የላይኛው መጋደያ” ተብሎ ተጠራ።
21
ጣዖቶቻቸውንም በዚያ ተዉ፤ ዳዊትና ሰዎቹም ወሰዱአቸው።
22
ፍልስጥኤማውያንም ደግሞ መጡ፤ ወደ ረዓይትም ሸለቆ ወረዱ።
23
ዳዊትም እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም፥ “በኋላቸው ዞረህ በሾላው ዛፍ ፊት ለፊት ግጠማቸው እንጂ አትውጣ።
24
በሾላውም ዛፍ ራስ ውስጥ የሽውሽውታ ድምፅ ስትሰማ፥ በዚያ ጊዜ እግዚአብሔር የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ ለመምታት በፊትህ ወጥቶ ይሆናልና በዚያ ጊዜ ፍጠን” አለው።
25
ዳዊትም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ከገባዖንም እስከ ጌሴራ ድረስ ፍልስጥኤማውያንን መታ።
← Chapter 4
Chapter 6 →