bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic 2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
/
1 Chronicles 12
1 Chronicles 12
Amharic 2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
1
በሴቅላቅም ከቂስ ልጅ ከሳኦል በተሸሸገ ጊዜ ወደ ዳዊት የመጡ እነዚህ ናቸው፤ በጦርነትም ባገዙት ኀያላን መካከል ነበሩ።
2
ቀስተኞችም ነበሩ፤ በቀኝና በግራም እጃቸው ድንጋይ ሊወነጭፉ፥ ፍላጻም ሊወረውሩ ይችሉ ነበር፤ ከብንያም ወገን የሳኦል ወንድሞች ነበሩ።
3
አለቃቸውም አኬዘር ነበረ፤ የጊብዓዊው የሰማዓ ልጅ ኢዮአስ፥ የዓዝሞት ልጆች ኢዮኤልና ፋሌጥ፥ በራኪያና ዓናቶታዊው ኢዩ፤
4
ገባዖናዊው ሰማያስ፥ እርሱ በሠላሳው መካከልና በሠላሳው ላይ ኀያል ሰው ነበረ፤ ኤርምያስ፥ ሕዝኤል፥ ዮሐናን፥ ገድሮታዊ ዮዛባት፤
5
ኤልዮዝ፥ ኢያሪሙት፥ በዓልያ፥ ሰማራያ፥ ሐሩፋዊው ሰፋጥያስ፤
6
ቆሬያውያን ሕልቃና፥ ኢሰያ፥ ዓዘርኤል፥ ዮዛር፥ ይሰከአም።
7
የግዶር ሰው የይሮሐም ልጆች ዮዔላ፥ ዝባድያ።
8
ዳዊትም በምድረ በዳ ውስጥ ባለችው በአንባዪቱ ሳለ ከጋድ ወገን የሆኑ እነዚህ ጋሻና ጦር የሚይዙ፥ ጽኑዓን፥ ኀያላን ሰልፈኞች፥ ወደ እርሱ ተጠጉ፤ ፊታቸውም እንደ አንበሳ ፊት ነበረ፤ በተራራም ላይ እንደሚዘልል ሚዳቋ ፈጣኖች ነበሩ።
9
አለቃው አዝር፥ ሁለተኛው አብድያ፥ ሦስተኛው ኤልያብ፤
10
አራተኛው መስመና፥ አምስተኛው ኤርምያስ፥
11
ስድስተኛው ኤቲ፥ ሰባተኛው ኤሊኤል፥
12
ስምንተኛው ዮሐናን፥ ዘጠነኛው ኤልዛባድ፥
13
ዐሥረኛው ኤርምያስ፥ ዐሥራ አንደኛው መክበናይ።
14
እነዚህ የጋድ ልጆች የጭፍራ አለቆች ነበሩ፤ ከእነርሱም ታናሹ የመቶ አለቃ ታላቁ የሺህ አለቃ ነበር።
15
በመጀመሪያው ወር ዮርዳኖስ ከዳር እስከ ዳር ሞልቶ በነበረ ጊዜ የተሻገሩት እነዚህ ናቸው፤ በሸለቆውም ውስጥ በምሥራቅና በምዕራብ በኩል የተቀመጡትን ሁሉ አባረሩ።
16
ዳዊትም ወደ ነበረባት ወደ አንባዪቱ ከብንያምና ከይሁዳ ወገን ሰዎች ዳዊትን ለመርዳት መጡ።
17
ዳዊትም ሊገናኛቸው ወጥቶ፥ “በሰላም ወደ እኔ መጥታችሁ እንደ ሆነ ልቤ ከእናንተ ጋር አንድ ይሆናል፤ ለጠላቶቼ አሳልፋችሁ ልትሰጡኝ መጥታችሁ እንደ ሆነ ግን፥ በእጄ ዓመፅ የለብኝምና የአባቶቻችን አምላክ ይመልከተው፥ ይፍረደውም፤” አላቸው።
18
መንፈስም በሠላሳው አለቃ በዓማሣይ ላይ መጣ፤ እርሱም፥ “ዳዊት ሆይ፥ እኛ ያንተ ነን፤ የእሴይ ልጅ ሆይ፥ እኛ ከአንተ ጋር ነን፤ ውጣ አምላክህ ይረዳሃልና ሰላም ሰላም ለአንተ ይሁን፤ ለሚረዱህም ሰላም ይሁን” አለ። ዳዊትም ተቀበላቸው፤ የጭፍራም አለቆች አደረጋቸው።
19
ዳዊትም ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሳኦልን ሊወጋ በመጣ ጊዜ ከምናሴ ወገን ሰዎች ወደ ዳዊት ከዱ፤ የፍልስጥኤማውያን አለቆች ግን፥ “በራሳችን ላይ ጉዳት አድርጎ ወደ ጌታው ወደ ሳኦል ይመለሳል” ሲሉ ተማክረው ሰድደውታልና እርሱ አልረዳቸውም።
20
ዳዊትም ወደ ሴቄላቅ ሲሄድ ከምናሴ ወገን የምናሴ ሻለቆች የነበሩ ዓድና፥ ዮዛባት፥ ይዲኤል፥ ሚካኤል፥ ዮዛባት፥ ኤሊሁና ጼልታይ ወደ እርሱ ከዱ።
21
ሁሉም ጽኑዓን ኀያላንና በሠራዊቱ ላይ አለቆች ነበሩና በአደጋ ጣዮች ላይ ዳዊትን አገዙት።
22
እንደ እግዚአብሔርም ሠራዊት ታላቅ ሠራዊት እስኪሆን ድረስ ዳዊትን ለመርዳት ዕለት ዕለት ይመጡ ነበር።
23
እንደ እግዚአብሔርም ቃል የሳኦልን መንግሥት ወደ እርሱ ይመልሱ ዘንድ በኬብሮን ሳለ ወደ ዳዊት የመጡት የሠራዊቱ አለቆች ቍጥር ይህ ነው።
24
ጋሻና ጦር ተሸክመው ለሰልፍ የተዘጋጁ የይሁዳ ልጆች ስድስት ሺህ ስምንት መቶ ነበሩ።
25
ለሰልፍ ጽኑዓን ኀያላን ሰዎች የነበሩ የስምዖን ልጆች ሰባት ሺህ አንድ መቶ ነበሩ።
26
የሌዊ ልጆች አራት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ።
27
የአሮንም ቤት አለቃ ዮዳሄ ነበረ፤ ከእርሱም ጋር ሦስት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ፤
28
ከእርሱም ጋር ጽኑዕ ኀያል ጐልማሳ ሳዶቅ ነበረ፤ ከአባቱም ቤት ሃያ ሁለት አለቆች ነበሩ።
29
የሳኦልም ወንድሞች ከሆኑ ከብንያም ልጆች ሦስት ሺህ ነበሩ። የሚበልጠው ክፍል የሳኦልን ቤት ይጠብቁ ነበሩ።
30
ጽኑዓን ኀያላን የሆኑ በአባቶቻቸውም ቤት የታወቁ የኤፍሬም ልጆች ሃያ ሺህ ስምንት መቶ ነበሩ።
31
በየስማቸው የተጻፉ ዳዊትን ያነግሡት ዘንድ የመጡ የምናሴ ነገድ እኩሌታ ዐሥራ ስምንት ሺህ ነበሩ።
32
እስራኤልም የሚገባውን ያደርግ ዘንድ ዘመኑን የሚያውቁ ጥበበኞች ሰዎች የይሳኮር ልጆች አለቆች ሁለት መቶ ነበሩ፤ ወንድሞቻቸውም ሁሉ ከእነርሱ ጋር ነበሩ።
33
በጭፍራውም ውስጥ ዳዊትን ለመርዳት የወጡ የተዘጋጁ፥ መሣሪያም ሁሉ የያዙ የዛብሎን ሰዎች አምሳ ሺህ ነበሩ፤ ከእነርሱ አንድስ እንኳ ደካማ አልነበረም።
34
የንፍታሌምም አለቆች አንድ ሺህ ነበሩ፥ ከእነርሱም ጋር ጋሻና ጦር የሚይዙ ሠላሳ ሰባት ሺህ ነበሩ።
35
ለሰልፍም የተዘጋጁ የዳን ሰዎች ሃያ ስምንት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ።
36
በጭፍራውም ውስጥ የሚወጡ፥ ለሰልፍም የተዘጋጁ የአሴር ሰዎች አርባ ሺህ ነበሩ።
37
በዮርዳኖስም ማዶ ካሉ ከሮቤልና ከጋድ ሰዎች ከምናሴም ነገድ እኩሌታ የጦር መሣሪያንም ሁሉ ይዘው የመጡ መቶ ሃያ ሺህ ነበሩ።
38
እነዚህ ሁሉ ዳዊትን በእስራኤል ሁሉ ላይ ያነግሡት ዘንድ አርበኞችና ሰልፈኞች እየሆኑ በፍጹም ልባቸው ወደ ኬብሮን መጡ፤ ደግሞም ከእስራኤል የቀሩት ሁሉ ዳዊትን ያነግሡት ዘንድ አንድ ልብ ነበሩ።
39
ወንድሞቻቸውም አዘጋጅተውላቸው ነበርና እየበሉና እየጠጡ በዚያ ከዳዊት ጋር ሦስት ቀን ተቀመጡ።
40
ደግሞም በእስራኤል ዘንድ ደስታ ሆኖአልና እስከ ይሳኮርና እስከ ዛብሎን እስከ ንፍታሌምም ድረስ ለእርሱ አቅራቢያ የነበሩ በአህያና በግመል በበቅሎና በበሬ ላይ እንጀራና ዱቄት የበለስ ጥፍጥፍና የዘቢብ ዘለላ የወይንም ጠጅ፥ ዘይትም በሬዎችንና በጎችንም፥ ፍየሎችንም በብዙ አድርገው ያመጡ ነበር።
← Chapter 11
Chapter 13 →